ቀጥታ፡

የግድቡ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ የበይ ተመልካች ሆና የቆየችበት ታሪክ ያከተመበት የስኬት ብስራት ነው - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ የበይ ተመልካች ሆና የቆየችበት ታሪክ ያከተመበት የስኬት ብስራት ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ መመረቁን ተከትሎ በወላይታ ሶዶ ከተማ በተደረገ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በግድቡ ግንባታ ወቅት የታየው አንድነት ሌላ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር አቅም ይሆናል ብለዋል።



 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ መመረቁ እኛ ኢትዮጵያውያን ታሪክ ሰሪ እንደሆንንና ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ ምሳሌ መሆናችንን ለዓለም ዳግም አረጋግጧል ነው ያሉት።

የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ የበይ ተመልካች ሆና የቆየችበት ታሪክ ያከተመበት የስኬት ብስራት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ለወል ትርክት ትኩረት በመስጠት በአንድነት በመንቀሳቀስ ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ከጅማሮው አንስቶ 2 ቢሊዮን ብር አስተዋፅኦ ማድረጉን አስታውሰው በህዳሴ ግድብ የታየውን ገድል በመድገም ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ጉዞን ዕውን ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የህዝቡ የዘመናት ቁጭት ምላሽ ያገኘበት ነው ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ናቸው።


 

ግድቡ የኢትዮጵያ የስኬት ታሪክ መገለጫ መሆኑን ገልጸው ሁሉንም ከዳር እስከ ዳር አንድ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉን የታደሙት ዳንኤል ታደመ እና ገብሬ ሌንጋ በበኩላቸው የህዳሴ ግድቡ በመመረቁ መደሰታቸውን ገልፀው ከግድቡ የተቀሰመውን ልምድ በመቀመር ሌላ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ግድቡ ከድህነት መውጫ፣ የልማት ፈር ቀዳጅና ለሀገሪቱ ዕድገት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አመልክተው በቀጣይም በመሰል ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፎ በማድረግ የድርሻቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ በወላይታ ሶዶ ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ የክልል፣ የዞን፣ የከተማ አስተዳደር እና የወረዳ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ነዋሪዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም