የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በራሳችን አቅም መልማትና መለወጥ እንደምንችል የተማርንበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በራሳችን አቅም መልማትና መለወጥ እንደምንችል የተማርንበት ነው

ዲላ/አርባ ምንጭ ፤መስከረም 8/2018 (ኢዜአ):- የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በራሳችን አቅም መልማትና መለወጥ እንደምንችል የተማርንበት እና ህብረታችንን ያረጋገጥንበት ነው ሲሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዲላና አርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
"በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሀሳብ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በማስመልከት የዲላና አርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን ገልፀዋል።
በሰልፉ ላይ ከተሳተፉ የከተማው ነዋሪዎች መካከል የዲላ ከተማ አካል ጉዳተኞች ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ማርታ ጤኮ ለኢዜአ እንዳሉት የግድቡ ተጠናቆ መመረቅ እንዳስደሰታቸው ለመግለጽ አደባባይ መውጣታቸውን ገልፀዋል።
''የግድቡ መጠናቀቅ በራስ አቅም ሰርተን ለመለወጥ የምናደርገውን ጥረት የሚያጠናክር ነው'' ያሉት ወይዘሮ ማርታ በቀጣይ አገራዊ ልማትን ለማፋጠን የሚያግዙ ስራዎች ላይ ለመሳተፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ስጦታው ተረፈ በበኩሉ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ከተባበርን መሻገር የማንችለው ተግዳሮት እንደሌለ አመላካች ነው ብሏል።
ግድቡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያለ ልዩነት ያስተሳሰረ የአንድነታችን ማሳያ መሆኑን ጠቅሶ አንድነታችንን ለላቀ ሃገራዊ ልማት ለመጠቀም መስራት አለብን ነው ያለው።
አቶ በቀለ ጊዶ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ለነገው ትውልድ የተሻለች ሃገር ለማውረስ ያስቻለ ነው ብለዋል።
የጌዴኦ ባህላዊ መሪ አባገዳ ቢፎም ዋቆ፤ ህዝቡ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ በቀጣይ በሚተገበሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የድርሻቸውን በመወጣት ጠንካራ አገር ለማፅናት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝም ተናግረዋል።
በተመሳሳይም "በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሃሳብ በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ሃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ግድቡ የአንድነታችን መገለጫ ነው ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኃይል ምንጭነት ባለፈ ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ብሎም የሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ ጉልህ ሚና የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ከጅማሮ አንስቶ እስከፍጻሜ ድረስ ላደረገው ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር)፤ አባቶች በአንድነት በአድዋ ድል እንዳስመዘገቡት ሁሉ የግድቡ መጠናቀቅ ይህ ትውልድ በልማት የሀገሪቱን ደማቅ ታሪክ መጻፍ ያስቻለ ነው ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁን በማስመልከት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ፣ ዲላ፣ ወላይታ ሶዶን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በተዘጋጀው የደስታ መግለጫ ሰልፍ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች እንዲሁም የተለያየ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።