ቀጥታ፡

የግድቡ ግንባታ በስኬት እንዲጠናቀቅ ያደረግነውን የተቀናጀ ድጋፍ በሌሎች ልማቶች ላይም እንደግማለን

ቡታጅራ ፤  መስከረም 8/2018(ኢዜአ) :-  ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት እንዲጠናቀቅ   ያደረግነውን የተቀናጀ ድጋፍ   በሌሎች  ልማቶች ላይ ለመድገም  የድርሻችንን እንወጣለን  ሲሉ የቡታጅራ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ ።

"በሕብረት ችለናል" በሚል መሪ ሀሳብ  የሕዳሴ ግድብ ምረቃን  በማስመልከት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቡታጅራ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ከተሳተፉት መካከል የከተማዋ ነዋሪዉ አቶ ሸምሱ ጀማል በሰጡት አስተያየት የሕዳሴ ግድብ በስኬት በመጠናቀቁ  ደስታዬ ወደር የለውም ብለዋል።

ይህም በጋራ ተቀናጅተን መልማት እንደምንችል  ማሳያ መሆኑን አመልክተው፤  ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ ያደረግነውን የተቀናጀ ድጋፍ በሌሎችም  ልማቶች ላይ ለመድገም የድርሻዬን እወጣለሁ ሲሉ ገልጸዋል።

ሌላኛዋ ወይዘሮ ሎሚ እሸቱ በበኩላቸው ፤ ለግድቡ ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ  አስታውሰው ፤ በስኬት በመጠናቀቁ ኩራትና ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል ።

የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ትዉልድ ተሻጋሪ አኩሪ ታሪክ ማኖር ስለመሆኑ ጠቅሰዉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተጀመሩ የልማት ስራዎች ሁሉ በመሳተፍ ሀገራቸዉን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማድረስ እንደሚተጉም ገልፀዋል ።

የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያንን እንደምንችል በተግባር ያሳየንበት አኩሪ ውጤታችን ነው ያለው ደግሞ ወጣት ወሊዩ ሻፊ ነው ።

ግድቡ የኤሌክትሪክ ሀይል ፍላጎት ለማሟላት የሚያግዝ ከመሆኑም ባሻገር  በተለይም ለወጣቱ ሰፊ   የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግሯል።

በየዘርፋችን ግድቡን ለማጠናቀቅ ያሳየነውን ቁርጠኝነትና ትብብር በሌሎች ሀገራዊ ልማቶች ለመድገም የበኩሌን እወጣለሁ ብሏል፡፡

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ከዘመናት ቁጭት የወጣንበት አኩሪ ተግባር ነው ብለዋል።

ለግድቡ ግንባታ  የዞኑ ማሕበረሰብ  በገንዘብና በቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ የግድቡ ስኬት  በቀጣይ ሌሎች  ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመስራት የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር  እንደሚያበረታታ ገልጸዋል።


 

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠዉ የግድቡ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያዊያን የአብሮነት፤ የፅናትንና የይቻላል መንፈስን ያጎለበተ   ነው ብለዋል።

አብሮነታችንን በማስጠበቅ ያሉንን የልማት አቅሞች ተጠቅመን  ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደምንችል አስተምሮናል፤ ለዚሕም መትጋት ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል።

በድጋፍ ሰልፉ የዞኑና  የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር  አመራሮች፣የሀይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም