የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገልግሎት ጥራት እና በደንበኛ እርካታ ላይ የማይናወጥ አቋሙን በተግባር እያሳየ ነው - አቶ መስፍን ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገልግሎት ጥራት እና በደንበኛ እርካታ ላይ የማይናወጥ አቋሙን በተግባር እያሳየ ነው - አቶ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገልግሎት ጥራት፣ በደንበኛ እርካታ እና በፈጠራ ላይ የማይናወጥ አቋሙን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እ.ኤ.አ በ2026 ለደንበኞች የሚያቀርባቸውን የበረራ ላይ ምግቦች ዝርዝር እና ቅምሻ መርሀ ግብር አከናውኗል።
በመድረኩ የግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰውን ጨምሮ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በአየር ትራንስፖርት ላይ የሚቀርቡ ምግቦች የመንገደኞችን ፍላጎትና ምርጫ ያማከሉ ናቸው።
ይህ ልዩ ዝግጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገልግሎት ጥራት፣ በደንበኛ እርካታ እና በፈጠራ ላይ ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ እንደመሆኑ መጠን የደንበኞቹን ፍላጎትና ምርጫ በሟላ መልኩ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረው፤ ይህን ማስተናገድ የሚያስችል መሰረተ ልማት በማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በተጨማሪም ዓለም ዓቀፍ የምግብ ባለሙያዎችን በመቅጠር የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ መሆኑን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የጠቆሙት።
አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን የሚያስቀጥሉ የተሳለጡ አገልግሎቶች መስጠቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ወቅት በምግብ አቅርቦት፣ ለምግብ ደህንነት እና ለአካባቢ አስተዳደር ስርዓቶች የተለያዩ ማረጋገጫዎች እንደተሰጡትም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ ጊዜያት በምርጥ የበረራ ላይ የምግብ አቅርቦት ማዕረግ ማሸነፉንና ይህ ማዕረግ ለመንገደኞች ምርጥ የበረራ ላይ ልምድ ለመስጠት የምናደርገውን ስራ እውቅና እና አድናቆት ያሳያል ብለዋል።