ቀጥታ፡

የጥራት አመራር ዓለም አቀፍ ዕውቅናዎች የኢትዮጵያ የከፍታ ህልም የማሳኪያ መንገዶች ናቸው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦ የጥራት አመራር ዓለም አቀፍ ዕውቅናዎች ኢትዮጵያ ከፍታዋን ለማረጋገጥ የያዘችውን ትልም ማሳኪያ መንገዶች መሆናቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በትምህርት ሥራ አመራር ሥርዓት ISO-21001-2018 ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱን ተከትሎ የምሥክር ወረቀት ርክክብ ተካሂዷል።


 

57 ዓመታትን ያስቆጠረው ኢንስቲትዩቱ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት የላቀ ሚና መጫወቱ ተገልጿል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ኢትዮጵያ በየዘርፎቹ እያካሄደች በሚገኘው ሪፎርም ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች የከፍታዋ መጀመሪያ ምልክቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሀገራችን ተቋማት የዓለም አቀፍ የጥራት አመራር ሥርዓት ዕውቅናዎች እያገኙ መሆናቸው የማንሰራራት ጉዞዋ ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሀገር አቀፍ የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየተደረገ ያለው ሪፎርም የሀገረ መንግስት ግንባታ አካል መሆኑንም ተናግረዋል።

በዘርፉ እየተገኙ ያሉ የጥራት አመራር ዓለም አቀፍ ዕውቅናዎች ኢትዮጵያ ከፍታዋን ለማረጋገጥ የያዘችው ትልም የማሳኪያ መንገድ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ጨምሮ በስሩ ያሉ ተቋማት 16 ዓለም አቀፍ ዕውቅናዎች ማግኘታቸውንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ተቋማት የተገልጋዩን እርካታ ማረጋገጥ አለባቸው ያሉት ሚኒስትሯ በቱሪዝም ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ሀገራዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የእውቅ ሙያተኞች መፍለቂያ መሆኑን በማውሳት፥ ኢትዮጵያ ያላትን ባህልና እሴት በአግባቡ በማስተዋወቅና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የበለጠ እንዲተጋ አስገንዝበዋል።


 

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱን አውስተዋል።

መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ ከስልጠና ባለፈ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እያደረገ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በዚህም የተገልጋዩን እርካታ መጨመር የሚችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።


 

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቱሪዝም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ዋነኛ መሰረት የሚሆን ዘርፍ ነው ብለዋል።

የሰው ሀብት፣ የመሰረት ልማት እንዲሁም የአሰራር ስርዓት መዘመን ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ፤ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ በመስራቱ የዕውቅና ምሥክር ወረቀት ማግኘቱን ገልጸዋል።


 

መንግስት ለምርትና አገልግሎት ጥራት በሰጠው ትኩረት የጥራት መንደር ገንብቶ ምርትና አገልግሎቶች ደረጃቸውን እንዲጠብቁ እያደረገ መሆኑንም አክለዋል።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በትምህርት ሥራ አመራር ሥርዓት ISO-21001-2018 ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም