ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራርና ሠራተኞች ለ15ኛ ጊዜ ደም ለገሱ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ አመራርና ሠራተኞች ለ15ኛ ጊዜ ደም ለግሰዋል፡፡

የኢዜአ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በሙያቸው ሀገርን ከማገልገል ባሻገር በተለያዩ የበጎ ተግባር ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ `ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

በዚህም የኢዜአ ሠራተኞች ደም መለገሳችን የወገንን ህይወት ይታደጋል በሚለው የዘወትር መርኃቸው ለ15ኛ ጊዜ በበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ መርሃ ግብር አከናውነዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የክልል ግንኙነት ቡድን መሪ ዮሐንስ ወንድይራድ፥ በተደጋጋሚ በማደርገው የደም ልገሳ የእናቶችና ህፃናትን ሕይወት ለመታደግ የበኩሌን በመወጣቴ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል ብሏል።

በተቋሙ የዲጅታል ሚዲያ የሀገር ውስጥ ቋንቋ የማህበራዊ ሚዲያ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሙሴ መለሰ በበኩሉ፤ የሚለግሰው ደም የወገኖቻችንን ህይወት የሚታደግ መሆኑን በመገንዘብ በተደጋጋሚ በመርሃ ግብሩ እየተሳተፈ መሆኑን ገልጿል።

የሚለግሰው ደም  የታማሚዎችን ህይወት ከመታደጉ ባሻጋር ለደም ለጋሾች በርካታ የጤና ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ የጤና ባለሙያዎችን መረጃ ዋቢ በማድረግ ተናግሯል፡፡

በኢዜአ የመረጃ ዴስክ ባለሙያ ናርዶስ ተክሌ የምትለግሰው ደም በተለይም በወሊድ ምክንያት የሚፈሰውን የእናቶችን ደም በመተካት በኩል የማይተካ ሚና አለው ብላለች፡፡

በተቋሙ የህግ አገልግሎት ከፍተኛ ቡድን መሪ የሆነው ሰለሞን ታደሰ በበኩሉ፤ ደም መለገስ የሌሎችን ህይወት ከመታደግ  በተጨማሪ የህሊና እርካታ እንደሚሰጥ ነው የገለጸው፡፡ 

ለመጀመሪያ ጊዜ ደም የለገሰው የተቋሙ የፊልም ኤዲተር ማስረሻ ዘርፉ በበኩሉ ደም መለገስ ከሰብአዊ ተግባር ባለፈ የሌሎችን ህይወት መታደግ ጭምር በመሆኑ ይህንን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የህግ የስነ-ምግባርና ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ዳይሬክተርና የፕሮግራሙ አስተባባሪ ታደለች ቦጋለ፤ የተቋሙ ሠራተኞች በየሶሰት ወሩ በቋሚነት ደም እየለገሱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ማንኛውም ጤነኛ ሰው ደም የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ህይወት ለመታደግ የደም ልገሳ በጎ ተግባርን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም