ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዓባይ ወንዝ ላይ የነበረውን ኢ-ፍትሐዊ ትርክት ቀይሯል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በመርህ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ አቋሟን እውን ያደረገችበትና በዓባይ ወንዝ ላይ የነበረውን ኢ-ፍትሐዊ ትርክት የቀየረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፣ በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፣ በአፍሪካ ካሪቢያን ሀገራት ማህበረሰብ የመሪዎች ስብሰባ እና በቀጣዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 80ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የዓለም ማህበረሰብንና የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበ ነው ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት የታየበት፣ በዓባይ ወንዝ ላይ የነበረውን ኢ-ፍትሐዊ ትርክት የቀየረ እና በአፍሪካውያን ዘንድ ዳግም መነቃቃትን የፈጠረ ታላቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በመርህ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ አቋሟን እውን ያደረገችበት ፕሮጀክት መሆኑን መግለጻቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የይቻላል መንፈስ ከቃል ወደ ተግባር የተቀየረበት ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ውጤታማ የፕሮጀክት አመራር ጥበብ የታየበት እንደሆነም ነው ያመላከቱት፡፡

በአፍሪካ የተለያዩ ተመራማሪዎች ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ያጠናቀቀችበት የፕሮጀክት አመራር ለሌሎች ልምድ እንደሚሆን አረጋግጠዋል ሲሉም አክለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በቀጣናው የምትጫወተውን ዲፕሎማሲያዊ ሚና እንደሚያሳድግ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ እና በአፍሪካ ካሪቢያን ሀገራት ማህበረሰብ ስብሰባ ላይ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኗን አምባሳደሩ አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ በሚካሄደው 80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የዓለም የስርዓተ ምግብ ጉባኤን ጨምሮ በአዲስ አበባ በተደረጉ ዓለም አቀፍ ሁነቶች እንዲሁም በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በምግብ ሥርዓት ሽግግር፣ በኮሪደር ልማት የተገኙ ውጤቶችን ቀምራ ታቀርባለች ብለዋል፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው ንቁ ተሳትፎ እንደምታደርግ ገልጸው፤ በተጓዳኝ አጋርነትን የሚያጠናክሩ ውይይቶችን እንደምታደርግም ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም