የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ መመረቁ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም የፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ መመረቁ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም የፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ መመረቁ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም የፈጠረ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ ገለፁ።
የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ "ከመቀነቷ" በሚል መሪ ሀሳብ ባዘጋጀውና ከ2ሺህ በላይ የመዲናዋ ሴቶች በተገኙበት የውይይት መድረክ አካሂዷል።
ውይይቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃትን ተከትሎ የታየውን መነሳሳት በሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ ዘላቂ በሆነ መንገድ መደገፍ የሚያስችል መነቃቃት ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል።
የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ መመረቁ ለመላው ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ደስታ ፈጥሯል።
በተለይ ሴቶች ግድቡ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ካላቸው ቀንሰው በመስጠትና ህዝቡን በማስተባበር የማይተካ ሚና ሲያበረክቱ መቆየታቸውንና ለዚህም ታላቅ አክብሮትና ምስጋና ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት።
የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ መመረቅ የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ያበሰረ፣ የመቻላችን ማሳያ እና ኢኮኖሚያዊ አቅምን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ወደ ቀጣይ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያንን የመቻል አቅም ያሳየ እና ኢትጵያውያን በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ አልፈው በትብብር ገድል የሰሩበት ነው ብለዋል።
በግድቡ መጠናቀቅ የተፈጠረውን መነሳሳት በሌሎች ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ለመድገም ሴቶችን ጨምሮ ሁሉም ሕብረተሰብ የበኩሉን እንዲወጣም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ቆንጂት ደበላ በበኩላቸው፥ የመዲናዋ ሴቶች ለግድቡ ግንባታ የበኩላቸውን አሻራ ማኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የእንጉርጉሮ ማብቂያና የኢትዮጵያ ማንሰራራት ማብሰሪያ መሆኑን በማንሳት፥ የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ መመረቅ በተለይም በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ለሚገኙ እናቶች ብርሀን የሚፈነጥቅ ነው ብለዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ ሴቶች በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ትልቅ ደስታ እና የይቻላል መንፈስ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
ለግድቡ መሳካት ያደረጉትን ተሳትፎ በሌሎች ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ለመድገም ቁርጠኛ መሆናቸው አረጋግጠዋል።