ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር የተዋወቀና ስራ ፈጣሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት ተደርጓል

ሀዋሳ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ):- በሲዳማ ክልል ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር የተዋወቀና ከራሱ ባለፈ ለሌሎች ስራ የሚፈጥር የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት መደረጉ ተገልጿል።

በክልሉ ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ፣ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች የተውጣጡ አሰልጣኞች የሚሰጠው የክህሎት ስልጠና ዛሬ በሀዋሳ ተጀምሯል።


 

በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀገረጽዮን አበበ እንዳሉት ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር የተዋወቀና ከራሱ ባለፈ ለሌሎች ስራ የሚፈጥር የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች የሚያሰለጥኗቸው ተማሪዎች የተሟላ ክህሎትና ዕውቀት እንዲኖራቸው በማድረግ ለሀገር ብልጽግና አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱንም እንዲሁ።

በክልሉ አዲሱን የትምህርትና ስልጠና ሪፎርም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ለውጦች የመጡ ቢሆንም የሚጠበቀውን ያህል አይደለም ያሉት ኃላፊዋ በአሰልጣኞች ያለውን የክህሎት ክፍተት በጥናት በመለየት ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ለሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር በኢንዱስትሪያላይዜሽን ላይ እየተከናወነ የሚገኘውን ተግባር ከግብ ለማድረስ የስልጠና ጥራት ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።


 

በፌዴራል ደረጃ የአሰልጣኞች ስልጠና የወሰደው የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ማኑፋክቸሪንግ ዲፓርትመንት መምህርና አሰልጣኝ መሳይ ተሾመ፤ የወሰደው ስልጠና ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ያስተዋወቀውና ያለበትን ክፍተት እንደሞላለት ገልጿል።

በስልጠናው ያገኘውን ዕውቀትና ክህሎት ከክልሉ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ለተውጣጡ ሰልጣኞች በማካፈል የተሻለ አቅም፣ ክህሎትና ዕውቀት የዳበረ ተማሪ ለማፍራት የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል።

ለ20 ቀናት በሚቆየው የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ ከክልሉ 14 ኮሌጆች የተውጣጡ 362 አሰልጣኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም