በሌማት ትሩፋት የተገኙ ስኬቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሌማት ትሩፋት የተገኙ ስኬቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሀዋሳ ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል በሌማት ትሩፋት የተገኙ ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በርብርብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሀም ማርሻሎ ገለፁ፡፡
የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ የ2017 የሥራ አፈፃጸም ማጠቃለያና በዘርፉ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ዞኖችና ወረዳዎች የዕውቅና መርሀ ግብር አካሄዷል፡፡
የሲዳማ ክልል መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሀም ማርሻሎ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት ሀገራዊው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከተጀመረበት ከ2015 ዓ.ም አንስቶ በክልሉ ለእንስሳት ሀብት ልማት ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
በዚህም በየዓመቱ እያደጉ የመጡ ስኬቶች የተመዘገቡ ሲሆን ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠልም በርብርብ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አብርሀም ገለፃ ባለፉት ዓመታት በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ በመኖ አቅርቦትና ጤና አጠባበቅ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
በዚህም ዝርያቸው የተሻሻሉ እንስሳት መጠንን ከነበረበት 6 በመቶ ወደ 18 በመቶ ማሳደግ፣ የእንስሳት መኖን ከማሳ እስከ ፋብሪካ ባሉ አማራጮች በብዛትና በጥራት ማምረት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
በዚህም የወተት ምርታማነት በመጨመሩ ለኢንዱስትሪዎችና ለገበያ በማቅረብ የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡
ፕሮግራሙን ከቤተሰብ ብልፅግና ኢኒሺየቲቭ ጋር በማስተሳሰር በወተት፣ በሥጋ፣ በዕንቁላል፣ በዓሣና በሌሎች ፓኬጆች መንደሮችን በማደራጀት ልማቱን የማስፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የክልሉ እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ ጆምባ በ2017 በጀት ዓመት በሁሉም የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው በ2018 በጀት ዓመት ተግባራቱን በእጅጉ የማሳደግ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በ2017 የተሰራጨውን 10 ሚሊዮን ዶሮ በተያዘው በጀት ዓመት ወደ 20 ሚሊዮን ለማሳደግ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቅሰው ከ258 ሺ በላይ የእንስሳት ዝርያ የማሻሻል ስራም ይሰራል ብለዋል፡፡
በዓሣ፣ በንብ፣ በበግና በፍየል እንዲሁም በሀር ልማትም የላቀ ውጤት ለማምጣት እየሰሩ መሆኑን አውስተዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይም የክልል፣ የዞኖችና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡