በቆላማ አካባቢ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት እየተገነቡ በሚገኙ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠቃሚ ሆነናል - አርብቶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በቆላማ አካባቢ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት እየተገነቡ በሚገኙ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠቃሚ ሆነናል - አርብቶ አደሮች

ጂንካ ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦ በአካባቢያቸው በመንግስት በሚገነቡ የመንገድ፣ የትምህርት፣ የጤና እና የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን የደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደሮች ተናገሩ።
ፕሮጀክቱ በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የማህበረሰቡን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በፕሮጀክቱ በግጦሽ ሳር ልማትና በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ፣ በእንስሳት ጤና አጠባበቅ እና የእንስሳት ምርታማነትን ማሻሻል፣ በግብርና ኤክስቴንሽን ስራዎችን በመሳሰሉ የማህበረሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ የአልቴ-አርጉዴ ቀበሌ ነዋሪ ባርጌ ዶዮ እና የኛንጋቶም ወረዳ የቻሬ-ኮፒሪያይ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ናስክሪያ ሎካፒቴ፤ በፕሮጀክቱ እየተከናወኑ በሚገኙ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ ሆነናል ብለዋል።
በፕሮጀክቱ የመንገድ፣ የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ግንባታዎች በመከናወናቸው የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል የአልቴ-አርጉዴ ቀበሌን ከዋናው መስመር የሚያገናኘው የ10 ኪሎ ሜትር መንገድ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የትምህርት ቤት እና የእንስሳት ህክምና ማዕከላትም መገንባታቸውን አንስተዋል።
በወረዳው የኮፕሪያይ ቀበሌ ነዋሪ ጃካ ፓርቾ፤ ከዚህ ቀደም በአካባቢው ጤና ጣቢያ ባለመኖሩ ከ21 ኪሎ ሜትር በላይ በእግር ይጓዙ እነደነበር አስታውሰው አሁን ላይ በአቅራቢያቸው በመገንባቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በቢሮው የቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሚሊዮን ተክሌ፥ ባለፉት ስድስት ዓመታት በክልሉ በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የማህበረሰቡን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ መሰራቱን ገልጸዋል ።
የመንገድ መሰረተ ልማት፣ የመጠጥ ውሃ፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት እና ሌሎችም በመገንባታቸው በአካባቢው ከ190 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤካል ነትር በበኩላቸው ቢሮው በአርብቶ አደሩ አካባቢ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን የሚቋቋም ማህበረሰብ ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአርብቶ አደሩ አካባቢ በርካታ ሀብቶችና ፀጋዎች ያሉ በመሆኑ በስፋት በማልማት ከተረጂነት ወደ አምራችነት የማሸጋገር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ እንድሪያስ ጌታ (ዶ/ር) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች በፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ተመልክተዋል።
በወቅቱም መንግስት በቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የድርቅ ተጋላጭነት በመቀነስ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ የልማት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።