ቀጥታ፡

የጤና አገልግሎትን እና የመረጃ ሥርዓትን በዲጂታል የማዘመን ተግባራት እየተከናወኑ ነው-ዶክተር መቅደስ ዳባ 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦የጤና አገልግሎትን በዲጂታል የታገዘ ለማድረግ፣ የመድሃኒትና የህክምና እቃዎች ስርጭትን በማዘመን ቀልጣፋ ተደራሽነትን የሚያረጋግጡ  ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የስማርት ዲጂታል ጤና አቅርቦት ሰንሰለት ሽግግርን ለመተግበር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።


 

ስምምነቱ በመላው ሀገሪቱ  የመድኃኒቶች እና የህክምና ዕቃዎች ፍሰትን የሚያቀላጥፍ ዘመናዊ፣ አስተማማኝ እና በመረጃ የተደገፈ የአቅርቦት ሰንሰለት ስርዓት  ለመዘርጋት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት፥ ሚኒስቴሩ ለማህበረሰቡ ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግና በሽታን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነትም የመድኃኒትና የህክምና አገልግሎትን ለህዝቡ በተሳለጠ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን እንደሚያጠናክር ጠቅሰዋል።

አጠቃላይ የጤና አገልግሎትን በዲጂታል የታገዘ ለማድረግ  እና  መረጃን በዘመናዊ  መልኩ ለመያዝ  የሚያስችሉ  ስራዎች  እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው ስምምነቱ ተቋማዊ የለውጥ ስራን የሚያቀላጥፍ ነው ብለዋል።


 

አገልግሎቱን የበለጠ ለማሳለጥና የመድሃኒት ስርጭትን በቴክኖሎጂ ለመቆጣጠር እንደሚያስችልም ነው ያነሱት።

የኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርፕራዝ ሶሉሽን ቺፍ ኦፍሰር አቶ ዮሐንስ ጌታሁን በበኩላቸው በስምምነቱ መሰረት በመላ ሀገሪቱ የመድኃኒቶች እና የህክምና ዕቃዎች ፍሰትን የሚያቀላጥፍ ዘመናዊ፣ አስተማማኝ እና በመረጃ የተደገፈ የጤና አቅርቦት ሰንሰለት ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።


 

አዲስ የሚተገበረው ስርዓት የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አሰራርን እንደሚያቀላጥፍም ነው ያነሱት።

የመድኃኒት ቁጥጥርና የንብረት ቆጠራ ሥርዓትን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፣ ጠንካራ የሃብት ደህንነት ቁጥጥር ለማድረግ እና የሕግ ተገዢነትን ለማረጋገጥ፣ ከግምጃ ቤት ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ያለውን የመድኃኒት ስርጭት የአገልግሎት ጥራትን እና ፍጥነትን ማረጋገጥ እንደሚያስችልም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም