ቀጥታ፡

የዓለም አቀፍ የጥራት አመራር ሥርዓት ዕውቅናዎች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ከፍታ ማሳያዎች ናቸው 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦የዓለም አቀፍ የጥራት አመራር ሥርዓት ዕውቅናዎች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ከፍታ ማሳያዎች መሆናቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በትምህርት ሥራ አመራር ሥርዓት ISO-21001-2018 ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱን ተከትሎ የምሥክር ወረቀት ርክክብ ተካሂዷል።

በዓለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ የምሥክር ወረቀት የዕውቅና ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽን ጨምሮ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።


 

በዚሁ ወቅት 57 ዓመታትን ያስቆጠረው የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት የላቀ ሚና መጫወቱ ተነግሯል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በሥነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ በቅርቡ ኢትዮጵያ ያስመረቀችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አይችሉም የተባለውን በህብረት እንደሚቻል ያረጋገጠ ተግባር ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ማሳያና ትውልዱን ታሪክ ከማውራት ታሪክ ወደ መስራት ያሸጋገረ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በየዘርፎቹ እያካሄደች በሚገኘው ሪፎርም ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች የከፍታዋ መጀመሪያ ምልክቶች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ጨምሮ በስሩ ያሉ  ተቋማት 16 ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘታቸውንም አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት የተገኙት የዓለምአቀፍ የጥራት አመራር ሥርዓት ዕውቅናዎች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ከፍታ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።

አገር አቀፍ የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየተደረገ ያለው ሪፎርም የአገረ መንግስት ግንባታ አካል መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ  ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ተቋማት የተገልጋዩን እርካታ ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶ ብላ በትኩረት እየሰራችባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ መሆኑን አመልክተው፤ ይህም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ከማፍራት ጀምሮ የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ በመገንባት ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱት አንቱታን ያተረፉ ባለሙያዎችን ያፈራ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ ያላትን ባህልና እሴት በአግባቡ በማስተዋወቅና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የበለጠ እንዲተጋ ጠይቀዋል።

ተቋማት እያገኙ ያለው ዓለም አቀፍ ዕውቅናም ለበለጠ ትጋት የሚጋብዝና ድርብ ሃላፊነት የሚጥል ነው ብለዋል። 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ሚናውን ሲጫወት መቆየቱን አውስተዋል።

መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ ከስልጠና ባለፈ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እያደረገ መሆኑንም ነው ያነሱት።

ኢንስቲትዩቱ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለውን የአስተዳደርና የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በመተግበር የአገልግሎት ጥራትን እያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም የተገልጋዩን እርካታ መጨመር የሚችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።

ዕውቅናው ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ ሊሰራ ያቀዳቸውን ስራዎች በላቀ ትጋትና ጥራት እንዲፈጽም መነቃቃት የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቱሪዝም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ዋነኛ መሰረት የሚሆን ዘርፍ ነው ብለዋል።

የሰው ሃብትና የመሰረት ልማት እንዲሁም የአሰራር ስርዓት መዘመንና መሰናሰን ለአገር ልማትና ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ያሟላ ምርትና አገልግሎት ለመስጠት ደረጃን መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ኢንስቲትዩቱ የሚሰጠውን አገልግሎት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መከወኑ በየጊዜው ሲፈተሽ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም ከሰው ሃይል ልማትና ከአሰራር ሥርዓት አኳያ በመመዘኛዎች ተፈትሾ የዓለም አቀፍ የጥራት ዕውቅና ማግኘቱን ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በቀጣይም የአገልግሎትና የአስተዳደር ጥራትን አስጠብቆ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።


 

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ፤ ኢንስቲትዩቱ የአመራር ሥርዓት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ በመስራቱ የዕውቅና ምሥክር ወረቀት ማግኘቱን ተናግረዋል።

መንግስት ለምርትና አገልግሎት ጥራት በሰጠው ትኩረት የጥራት መንደር ገንብቶ ምርትና አገልግሎቶች ደረጃቸውን እንዲጠብቁ እያደረገ ነው ብለዋል።

ከዚህ አኳያ ኢንስቲትዩቱን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቀ ምርትና አገልግሎት መስጠታቸው እየተፈተሸ ዕውቅና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በትምህርት ሥራ አመራር ሥርዓት ISO-21001-2018 ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም