የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን በመጪው ህዳር መጨረሻ ለመጀመር እቅድ ተይዟል - ኢዜአ አማርኛ
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን በመጪው ህዳር መጨረሻ ለመጀመር እቅድ ተይዟል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን በ2018 ዓ.ም ህዳር መጨረሻ ለመጀመር እቅድ መያዙን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ በመረቁበት ወቅት የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በአዲሱ ዓመት ከሚጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የኢትዮጵያን የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ወደ ላቀ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም አፍሪካውያንን ከመላው ዓለም ጋር ለማገናኘት ፣ቱሪስቶች እና ኢንቨስተሮችን ለመሳብ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
አውሮፕላን ማረፊያው አየር መንገዱ በአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት እየተጫወተ ያለውን ግንባር ቀደም ሚና የበለጠ እንደሚያሳድገው አመላክተዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ለመጀመር የሚያስችሉ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።
የግንባታውን የመጀመሪያ ደረጃ ስራ ለማከናወን የኮንትራክተሮች መረጣ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን በህዳር ወር መጨረሻ ለመጀመር እቅድ መያዙን አመላክተዋል።
አየር መንገዱ ባለፈው አንድ አመት ተኩል ከቦይንግ እና ኤርባስ በርካታ አውሮፕላኖች ማዘዙን አስታውሰው ከነዚህ መካከል እኤአ 2026 አገልግሎት ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀው ቦይንግ 777-9 እንደሚገኝበት ገልጸዋል፡፡
አየር መንገዱ ያዘዛቸውን 20 ቦይንግ 777-9 አውሮፕላኖችን ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ መረከብ እንደሚጀምር ገልጸው ይህም አየር መንገዱን አውሮፕላን ካዘዙ ጥቂት አየር መንገዶች መካከል አንዱ ያደርገዋል ብለዋል።
አየር መንገዱ እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመጠቀም አሰራሩን እያቀላጠፈ መሆኑን ገልጸው የአዲሶቹ የቦይንግ አውሮፕላኖች ትዕዛዝም የዚሁ አካል መሆኑን አስታውቀዋል።
የሲቢኢ ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አየር መንገዱ ለያዘው ግብ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
ከመላው ዓለም ወደ አፍሪካ ለሚመጡ እንዲሁም ከአፍሪካ ወደ ተቀረው ዓለም ለሚሄዱ መንገደኞች አንደኛው መግቢያ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
25 ሚሊዮን መንገደኞች በዚህ አየር ማረፊያ እንደሚያልፉ ገልጸው፥ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ መገንባት የመንገደኞችን ቁጥር ወደ መቶ ሚሊዮን በማሳደግ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያመጣ ጠቁመዋል።
ከሌሎች ትልልቅ የአውሮፕላን ማረፊያ ካላቸው ሀገራት ጋር ለመወዳዳር እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።
በተለያዩ ሀገራት ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ መሰረተ ልማቶች ለኢኮኖሚያዊ እድገት መሰረት መሆናቸውን በመግለፅ፥ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ የኢትዮጵያን እንዲሁም የአፍሪካን ኢኮኖሚ የማሳደግ አቅም እንደሚኖረው አመላክተዋል።