ቀጥታ፡

ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በጋ የሆኑ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በታች የዝናብ  ስርጭት ይኖራቸዋል

አዳማ ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦- ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በጋ  የሆኑ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በታች የዝናብ  ስርጭት እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ የክረምት ወቅት የአየር ጸባይ ትንበያ ግምገማና የበጋ ወቅት የአየር ሁኔታ ጸባይ አዝማሚያ ትንበያ ይፋ ለማድረግ ያዘጋጀው መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንዳስታወቁት ኢንስቲትዩቱ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የአየር ትንበያ መረጃዎችን በወቅቱ ለተጠቃሚዎች እየሰጠ ይገኛል።


 

ትንበያዎቹ ለግብርና፣ ለውሀ ሀብት አስተዳደር፣ ለአደጋ ስጋት ዝግጅት፣ ለጤናና ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እያገለገሉ መሆናቸውን  ገልፀዋል።

የትንበያዎቹን ትክክለኛነት ለማሳደግም ሳይንሳዊ ዘዴን በመጠቀም መሰራታቸውን ጠቁመው ይህም የኢንስቲትዩቱን በ2017/18 የክረምት ወቅት የአየር ጸባይ ትንበያ  ውጤታማ እንዳደረገው ገልጸዋል።

አሁን ላይ  ኢኒስቲትዩቱ የበጋ ወቅት ትንበያ መረጃዎችን ለህብረተሰቡና ለተቋማት ይፋ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በጋ በሆኑት የቦረናና ጉጂ ዞኖች፣ ሲዳማና ደቡብ ኢትዮጵያ መደበኛ ዝናብ እንደሚኖራቸው ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

እንዲሁም የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ክፍል ደግሞ ከመደበኛ በታች የሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚያገኙ አክለዋል።

በሌላ በኩል የምእራብና ደቡብ ምእራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ አቶ ፈጠነ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ እነዚህን መረጃዎች  በመጠቀም የአደጋ ተጋላጭነትን በመቀነስ ስጋቶችን ወደ መልካም አጋጣሚዎች በመቀየር ምርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ አስገንዝበዋል።

የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትር (ዶ/ር) ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ መረጃን በማዘመን እየሰጠ ያለው ትንበያ ለተለያዩ ተቋማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልፀዋል።


 

በተለይ ሴክተር ተኮር መረጃን በወቅቱ ለተጠቃሚዎች በመስጠት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው ገልፀዋል።

በተለይ በውሀ ሴክተሩ የሚቀርቡ መረጃዎችን ሚኒስቴሩ በአግባቡ በመጠቀም የታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ የውሀ ሙሌትን በተሳካ ሁኔታ ማከናወኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የሚሰጡትን ትንበያዎች በአግባቡ በመተንተንና ተግባር ላይ ለማዋል ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች እንዲጠቀሙበት ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።

በመድረኩ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሁሉም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና ምክትል ሰብሳቢዎች፣ የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ  ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም