በትምህርት ውጤታማ መሆን የሚቻለው የሚባክን ጊዜ ሳይኖር በርትቶ በማጥናት ብቻ ነው-ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት ውጤታማ መሆን የሚቻለው የሚባክን ጊዜ ሳይኖር በርትቶ በማጥናት ብቻ ነው-ተማሪዎች

መቀሌ ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦ በትምህርት ውጤታማ መሆን የሚቻለው የሚባክን ጊዜ ሳይኖር በርትቶ በማጥናት ብቻ ነው ሲሉ በመቀሌ የቃላሚኖ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ።
ትምህርት ቤቱ ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ያስፈተናቸው ተማሪዎች በሙሉ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት እንዳስመዘገቡም አመልክቷል።
ተማሪዎቹ እንዳሉት፤ ውጤት ለትምህርት ሙሉ ጊዜ በመስጠትና በተለየ ትጋትና ጥረት እንጂ ጊዜን ያለ አግባብ በማባከን አይመጣም።
ከትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ካለፉ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሰምሃል ጌታቸው፤ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመግባት የሚያስችላትን 574 ነጥብ እንዳስመዘገበች ገልፃለች።
በትምህርት ውጤታማ መሆን የሚቻለው የሚባክን ጊዜ ሳይኖር ያለመታከት በትጋት በርትቶ በማጥናት በመሆኑ በዚህ መልኩ ለስኬት መብቃቷን ተናግራለች።
ሌላኛው የትምህርት ቤቱ ተማሪ አዶናይ ገብረስላሴ፤ በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና 572 ነጥብ በማምጣት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመግባት መዘጋጀቱን ተናግሯል።
በተመሳሳይ ጥረት ለውጤት መብቃቱን የተናገረው ተማሪው በቀጣይም ለላቀ ስኬት መዘጋጀቱን ገልጿል።
ተማሪዎች የተማሩትን ትምህርት ወዲያውኑ በማንበብ ያገኙትን ግንዛቤ ሊያሳድጉት እንደሚገባና ይህንንም ሳይሰለቹ በመተግበር ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ መልእክቱን አስተላልፏል።
የ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ አገር አቀፍ ፈተና 568 ያመጣው ተማሪ አንገሶም ደሳለኝ በበኩሉ፣ በመምህራን እገዛ በራሱ ጥረትና ልፋት ለውጤት መብቃቱን ተናግሯል።
የመቀሌ ቃላሚኖ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና የወሰዱ 175 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያስገባ ውጤት ማስመዝገባቸውም ተመልክቷል።