ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል በትምህርቱ ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሐረር ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል በትምህርቱ ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

"በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥራት ያለው ትምህርት ለሀገር ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ በክልሉ የትምህርት ጉባዔ መካሄድ ጀምሯል።


 

በጉባዔው መክፈቻ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ባደረጉት ንግግር በክልሉ በትምህርት ተሳትፎ፣ በጥራት፣ በተማሪዎች ውጤት እና በሌሎች የትምህርት ዘርፎች አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።

በክልሉ ባሉ ወረዳዎች ፍትሃዊ የትምህርት ተሳትፎን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎችም በተማሪዎች ውጤት ላይ ለውጥ እያሳዩ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

ለዚህም በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በክልሉ የሚመዘገበው ውጤት በየዓመቱ እድገት እያሳየ መምጣቱን በማሳያነት አንስተዋል።

ለውጤቱ መሻሻልም የትምህርት አመራሩ፣ የመምህራን፣ የተማሪዎችና ወላጆች የተቀናጀ ሥራ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይም በተለይም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ የማድረግ እንዲሁም መጠነ ማቋረጥና የትምህርት መድገም ችግሮችን የመቅረፍ ስራ ይከናወናል ብለዋል።

እንዲሁም በክልሉ በከተማም ሆነ በገጠር ወረዳዎች ባሉ ትምህርት ቤቶች የሚታዩ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ብክነት እንዳይኖርና የትምህርት ጥራትን ይበልጥ የማረጋገጥ ስራ ትኩረት የሚሰጠው ነው ብለዋል።

የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ የማሳደግና ሌሎች በትምህርት ዘርፉ የታዩ ውስንነቶችን የመፍታትና ጥንካሬዎችን የማስቀጠል  ስራም ይከናወናል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ዓመታት የትምህርት ተሳትፎን በማሻሻልና ፍትሃዊነቱን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ስራ ተከናውኗል።


 

በተለይም በትምህርት ለትውልድ፣ በተማሪዎች ምገባ እና በሌሎችም መርሃ ግብሮች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፤  በ2018 የትምህርት ዘመንም ይኸው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በክልሉ የትምህርት ዘርፉን ስብራት በመጠገን በተከናወነው ስራ በእውቀት፣ በክህሎትና በስነ ምግባር የታነጹ ዜጎችን የማፍራት ስራ ተከናውኗል ያሉት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ነገዎ ናቸው።


 

በተለይም በክልሉ በ6ኛ፣ በ8ኛ እና በ12ኛ ክፍል ክልላዊና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች የተማሪ ውጤት በየዓመቱ መሻሻል ማሳየቱን  ተናግረዋል።

ጉባዔውም በትምህርት ዘርፉ የታዩ ጥንካሬዎችና ድክመቶችን በመገምገም በ2018 የትምህርት ዘመን የተሻለ ስራ ለማከናወን ታልሞ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በጉባዔው የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር፣ በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ፣ የክልሉ አመራሮች፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም