ቀጥታ፡

በጋምቤላ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ 

ጋምቤላ/ጂንካ ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ።

ወባ በስፋት ከሚስተዋልባቸው የአገሪቷ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ጋምቤላ ክልል የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።


 

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አቤል አሰፋ በክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት በክልሉ የማህበረሰብ ጤና ችግር የሆነውን የወባ በሽታ የመከላከሉን ስራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተከናወኑት ዘርፈ ብዙ ስራዎች በሽታው በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ተፅዕኖ መቀነስ ቢቻልም ማስወገድ ያለመቻሉን ተናግረዋል።


 

በመሆኑም የጤና ሚኒስቴር ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር ባደረገው የተቀናጀ ጥረት በሽታውን የመከላከሉን ስራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት በሀገር አቀፍ ብሎም በክልሉ ደረጃ ዛሬ እንዲጀመር መደረጉን ገልጸዋል።

በክልሉ የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት የሚሰጠው ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ 11 ወረዳዎች መሆኑን ጠቁመው ክትባቱ ከመደበኛው የክትባት መርሃ ግብር ጋር ተቀናጅቶ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ክትባቱ የሚሰጠው እድሜያቸው ከ5 ወር እስከ 11 ወር ለሆኑ ህፃናት መሆኑን ጠቁመው ለክትባት መርሃ ግብሩ ስኬታማነት የወላጆችና የማህበረሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ኃላፊው  አሳስበዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ አቦር አሌክስ፤  የወባ በሽታ የክልሉ ቀዳሚው የጤና ችግር መሆኑን ተናግረዋል። 


 

በመሆኑም መንግስት ለጤናው ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመቀናጀት ከሌሎች የወባ መከላከያ ስራዎች በተጨማሪ የበሽታው መከላከያ ክትባት መስጠት መጀመሩ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል። 

ስለሆነም ለክትባት መርሃ ግብሩ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ አቦር አሳስበዋል።

በክልሉ ዛሬ በይፋ በተጀመረው የወባ መከላከያ ክትባት መርሃ ግብር እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ 14 ሺህ 417 ህፃናትን ተደራሽ ለማድረግ ግብ መቀመጡም ተገልጿል።

በተመሳሳይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በተገኙበት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀምሯል።


 

ክትባቱ የወባ ስርጭት ባለባቸው ወረዳዎች እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን በዘመቻው ህፃናት ክትባቱን እንደሚወስዱም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም