የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ራስን የመቻል ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ራስን የመቻል ማሳያ ነው

ወልቂጤ ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ራስን የመቻልና የማንሰራራት ምልክት መሆኑ ተመላከተ።
"በሕብረት ችለናል" በሚል መሪ ሀሳብ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁን አስመልክቶ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ እና ቀቤና ልዩ ወረዳ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄዷል፡፡
በድጋፉ ሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሐመድ ኑርዬ (ዶ/ር) በዚሕ ወቅት እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ራስን የመቻል ማሳያና የኢትዮጵያ ማንሰራራት ጅማሮ ምልክት ነው፡፡
''ግድቡ ወደ ልማት ለምናደርገው ጉዞ ጠንካራ መሠረት ነው፤ መንግስት የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረትም አዎንታዊ አበርክቶ ያለው ትልቅ ፕሮጀክት ነውም ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብ ከተባበርን የማናሳከው ስራ እንደሌለ ያሳየን ዳግማዊ ዓድዋ ነው ብለዋል፡፡
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተሳተፉት ወይዘሮ አፀደ ሳሕሌና አቶ ታሪኩ ወልደማርያም፤ የሕዳሴ ግድብ ስኬትን በሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲደገም እንደግፋለን ብለዋል።
የግድቡ ውጤት የተፈጥሮ ሀብቶችን ለልማት ለማዋል ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የታደሙ የቀቤና ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለዚሕ መብቃት ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።
ከሰልፉ ተሳታፊዎቹ መካከል ወጣት ፈቲያ ሱልጣን፤ የኢትዮጵያውያን ሕብረት ጎልቶ የታየበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በመጠናቀቁ መደሰቷን ገልፃለች።
የግድቡ መጠናቀቅ የታሰቡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በአንድነት ለማከናወን መነሳሳት የሚፈጥር ነው ስትል አክላለች።
አቶ ሙዴ ዳዋ በበኩላቸው፤ የሕዳሴ ግድቡ ለስኬት መብቃት በራስ አቅም በጋራ መስራት እንደምንችል ያሳየንበት እና አንድነታችንን ያጠናከረ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ይሕም በቀጣይም በትልልቅ የልማት ስራዎች የሚጠበቅብንን ሁሉ በመፈጸም ማሳካት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው ሲሉም ተናግረዋል ።
የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኤዶሳ ፤ የግድቡ መገንባት ሌሎች ፕሮጀክቶችም በስኬት እንዲጠናቀቁ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በበኩላቸው፤ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ሌሎች ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን የመስራት አቅም እንዳለን የታየበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በድጋፍ ሰልፉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።