ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የድህረ-ምርት ብክነትን ከአምስት በመቶ በታች መቀነስ የሚያስችል ስትራቴጂ ተግባራዊ ተደርጓል 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የድህረ-ምርት ብክነትን ከአምስት በመቶ በታች መቀነስ የሚያስችል ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። 

በኢትዮጵያ የድህረ-ሰብል አያያዝና ሜካናይዜሽን ማዕከል የማቋቋም ድጋፍ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ አውደ ጥናት በመካሄድ ላይ ይገኛል። 

ፕሮጀክቱ በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትና በኦስትሪያ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ፥ እንዲሁም በግብርና፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ቦኩ ዩኒቨርሲቲ ትብብር እንደሚተገበር ተገልጿል። 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ተወካይና አማካሪ ፕሮፌሰር አሊ መሀመድ፥ የድህረ-ምርት አያያዝ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ ቀልጣፋና አካታች የምግብ ስርዓት ለመገንባት በምታደርገው ጥረት ወሳኝ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል። 

ፕሮጀክቱ በድህረ-ምርት አሰባሰብ ሂደት በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እና በእንስሳት ተዋጽኦ የሚደርሰውን ከፍተኛ ብክነት ለመቀነስ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ በረጅም ጊዜ ግብ የድህረ-ምርት ብክነት ከአምስት በመቶ በታች መቀነስ የሚያስችል ብሔራዊ ስትራቴጂ ተግባራዊ በማድረግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ፥ የድህረ-ምርት ሥርዓት መጠናከር ለአግሮ ኢንዱስትሪ ምርታማነትና ጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል። 

በኢንዱስትሪ ዘርፍ በኢትዮጵያ ታምርትና የኢትዮጵያን ይግዙ ተነሳሽነት የግብርና ሽግግርን ማሳለጥ የሚያስችል ስኬታማ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

ይህም በአግሮ-ኢንዱስትሪ ዕድገት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በወጪ ንግድና ተኪ ምርት ተጨባጭ ውጤት እንዲመዘገብ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ናፕ (ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያና ኦስትሪያ በወዳጅነትና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ብለዋል። 

የድህረ-ሰብል አያያዝና ሜካናይዜሽን ማዕከል የማቋቋም ድጋፍ ፕሮጀክት የኢትዮ-ኦስትሪያን ጠንካራ አጋርነት በማስቀጠል ለምግብ ዋስትና እና ዘላቂ የግብርና ዕድገት የጋራ ቁርጠኝነትን እንደሚያሳይ ጠቅሰዋል። 

ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ የወደፊት ዕድገት ወሳኝ ለሆነው የግብርና ምርታማነት ተጨማሪ አቅም መሆኑን ተናግረዋል። 

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ምክትል ተወካይ አሰግድ አዳነ፥ የድህረ-ሰብል አያያዝና ሜካናይዜሽን ማዕከል የማቋቋም ድጋፍ ፕሮጀክት በግብርና ምርታማነት ዕሴት ሰንሰለት ውስጥ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል። 

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ እይታ፣ የድህረ-ሰብል አያያዝ ሁኔታ፣ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሚና ለድህረ-ሰብል አያያዝ፥ የግብርና የንግድ ሥርዓትና የዲጂታል ግብርና ልምዶችን በሚዳስሱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም