ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የመቻል አቅማችንን ያሳየና ለሌሎች የልማት ሥራዎች የላቀ መነሳሳትን የፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የመቻል አቅማችንን ያሳየና ለሌሎች የልማት ሥራዎች የላቀ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ ገለፁ።

አቶ ሞገስ ይህን ያሉት የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ "ከመቀነቷ" በሚል መሪ ሀሳብ ባዘጋጀውና ከ2 ሺህ በላይ የመዲናዋ ሴቶች በተገኙበት የውይይት መድረክ ላይ ነው።


 

ውይይቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃትን ተከትሎ የታየውን መነሳሳት በሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመደገፍ የሚያስችል መነቃቃት ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል።

የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለመላው ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ደስታ ፈጥሯል።

በተለይ ሴቶች ግድቡ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ካላቸው ቀንሰው በመስጠትና ህዝቡን በማስተባበር የማይተካ ሚና ሲያበረክቱ ቆይተዋል ነው ያሉት።


 

የግንባታው መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ያበሰረ፣ የመቻላችን ማሳያ እና ኢኮኖሚያዊ አቅምን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ወደ ቀጣይ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡

በግድቡ መጠናቀቅ የተፈጠረውን መነሳሳት በሌሎች ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ለመድገም ሴቶችን ጨምሮ ሁሉም ሕብረተሰብ የበኩሉን እንዲወጣም አፅንኦት ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ቆንጂት ደበላ በበኩላቸው፥ የመዲናዋ ሴቶች ለግድቡ ግንባታ የበኩላቸውን አሻራ ማኖራቸውን ጠቅሰዋል።


 

የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ በተለይም በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ለሚገኙ እናቶች ብርሀን የሚፈነጥቅ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም