ልዩ አዳሪ ትምሕርት ቤቱ ተማሪዎችን ለላቀ ውጤት የሚያበቁ ተግባራትን አጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ልዩ አዳሪ ትምሕርት ቤቱ ተማሪዎችን ለላቀ ውጤት የሚያበቁ ተግባራትን አጠናክሮ ቀጥሏል

ደሴ ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦ በትምሕርት ቤቱ የሚማሩ ተማሪዎችን ለላቀ ውጤት ከማብቃት ባሻገር ተወዳዳሪነታቸውን የሚያጎለብቱ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠሉን የይሁኔ ወልዱ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት አስታወቀ።
በትምህርት ቤቱ በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ሁሉም ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያስችል ውጤት ማስመዝገባቸውም ተመልክቷል።
የይሁኔ ወልዱ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ፍቅር በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በሀገርና በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየሰራ ነው።
ተማሪዎችን ለላቀ ውጤት ከማብቃት ባሻገር ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ በቴክኖሎጂና በማካካሻ ትምህርት የታገዘ እውቀትና ክህሎታቸውን የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተዋል።
በዚህም በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ከፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ 51 ተማሪዎች ሁሉም የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ማምጣታቸውን አስታውቀዋል።
ከተፈተኑት ውስጥም 33ቱ ተማሪዎች ከ500 በላይ ውጤት ሲያመጡ ቀሪዎቹም በየደረጃው የተሻለ ውጤት ማስመዝገባቸውን አረጋግጠዋል።
በአዲሱ የትምህርት ዘመንም ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ 95 አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል 373 ተማሪዎችን ሲያስተምር መቆየቱን አውስተው፤ በተያዘው የትምህርት ዘመንም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ 89 ተማሪዎችን እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
በትምህርት ቤቱ የታሪክ መምህር አሰፋ ተሾመ በበኩላቸው፤ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ትልቅ ደረጃ እንዲደርሱ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችም በቴክኖሎጂ በመታገዝ እንዲያጠኑ በማድረግ፣ ማካካሻ ትምህርት በመስጠትና ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በ2017 የትምህርት ዘመን ሀገር አቀፉን ፈተና ወስደው ውጤታማ በሆኑት የትምህርት ቤት ተማሪዎች መኩራታቸውን አንስተው፤ በቀጣይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትጋት እንሰራለን ብለዋል።
ተማሪዎችን በማገዝ፣ ያልገባቸውን ደጋግመው በማስረዳትና አጋዥ መጽሐፍትን በመጠቆም በሰራነው ስራ የመጣው ውጤት አስደስቶናል ያሉት ደግሞ የትምህርት ቤቱ የስነ-ህይወት መምህር አማረ ሰጠ ናቸው።
ቀጣይም የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ሀገርና ህዝባቸውን ማገልገል እንዲችሉ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
የይሁኔ ወልዱ ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በ2016 የትምህርት ዘመን 68 ተማሪዎች በማስፈተን የተሻለ ውጤት አስመዝግበው ማለፋቸውን ከትምህርት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።