የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የኢትዮጵያ የከፍታና የማንሰራራት ጉዞ ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የኢትዮጵያ የከፍታና የማንሰራራት ጉዞ ማሳያ ነው
ዲላ፤ መስከረም 8/2018 (ኢዜአ) :- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የኢትዮጵያ የከፍታና የማንሰራራት ጉዞ ማሳያ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዲላ ክላስተር አስተባባሪ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር ) ገለጹ።
የሕዳሴ ግድብ መመረቅን በማስመልከት በዲላ ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዲላ ክላስተር አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር )፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የኢትዮጵያ የከፍታና የማንሰራራት ጉዞ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የግድቡ መገንባት የመቻል አቅም የታየበት መሆኑን በማንሳት ከድህነት አዙሪት በመውጣት የኢትዮጵያን የብልፅግና ስኬት አይቀሬነት ያረጋገጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም ለዚህ ስኬት በመብቃታችን ደስታው የጋራችን በመሆኑ ሁላችንም እንኳን ደስ ያለን የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሕብረት በመቆም በፅናትና በትጋት ያሳካነው ግድብ በመሆኑ ደስታችን የጋራ ነው ብለዋል።
የዞኑ ሕዝብ ለግድቡ ግንባታ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አውስተው፤ በቀጣይም ግዙፍ ሃገራዊ ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙ የከተማዋ ነዋሪዎችም በራሳችን ጥሪትና በልፋታችን ለስኬት ያበቃነው ግዙፍ ፕሮጀክት በመሆኑ ተደስተናል ብለዋል።