ቀጥታ፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በአፍሪካውያን ዘንድ ዳግም መነቃቃትን  የፈጠረ ታላቅ ድል ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የይቻላል መንፈስን ከቃል ወደ ተግባር በመቀየር በአፍሪካውያን ዘንድ ዳግም መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ የውጭ ግንኙነት ተግባራት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ነብያት በመግለጫቸው፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅ የዓለምን ማህበረሰብና የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበ ነው ብለዋል።

የግድቡ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት የታየበት መሆኑን የገለፁት አምባሳደር ነብያት፤ በአፍሪካውያን ዘንድ ዳግም መነቃቃትን የፈጠረ ታላቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የይቻላል መንፈስ ከቃል ወደ ተግባር የተቀየረበት መሆኑን በማንሳት፥ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ውጤታማ የፕሮጀክት አመራር ልምዷን ለሌሎች የምታካፍልበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በአፍሪካና በቀጣናው የምትጫወተውን ዲፕሎማሲያዊ ሚና የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

አምባሳደር ነብያት በመግለጫቸው ኢትዮጵያ በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ እና በአፍሪካ ካሪቢያን ሀገራት ማህበረሰብ ስብሰባ ላይ ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኗን አውስተዋል።

በቀጣይ በሚካሄደው 80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ እንደምታደርግም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የስርዓተ ምግብ ጉባኤን ጨምሮ በአዲስ አበባ በተደረጉ ዓለም አቀፍ ሁነቶች የተገኙ ውጤቶችን ቀምራ እንደምታቀርብም ነው የጠቀሱት።

ከተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በተጓዳኝ አጋርነትን የሚያጠናክሩ ውይይቶችን እንደምታደርግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም