ቀጥታ፡

በሞተር የሚሰሩ ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲገቡ መፈቀዱ የውሃ ቱሪዝምን ለማሳደግ ወሳኝ እርምጃ ነው -ቱሪዝም  ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት በሞተር የሚሰሩ ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መፍቀዱ የውሃ ቱሪዝምን ለማሳደግ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የቱሪዝም  ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መስህብ አማራጮች ቢኖሯትም በውስን ዘርፎች ላይ ብቻ በማተኮር ስትሰራ መቆየቷ ይታወቃል፡፡

ለዘርፉ ዕድገት እምቅ አቅም ያለውን የውሃ ቱሪዝምን በአግባቡ ለመጠቀም የገንዘብ ሚኒስቴር በሞተር የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ፈቅዷል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፣ ከለውጡ ወዲህ የቱሪዝም ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን አስተዋፅኦ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶታል።

ይህም መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን ከዕድገት ምሰሶዎች አንዱ በማድረግ የፖሊሲ እና የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያገኝ አድርጓል ብለዋል።

በዚህም መሰረተ ልማት ማሟላት፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስፋፋት እና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ  የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።

የሞተር ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲገቡ መፈቀዱ መንግሥት ለዘርፉ እድገት ቀጣይነት የሰጠውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።  

ለቱሪዝም መዳረሻ ልማት መስፋፋት ከሰጠው ትኩረት ባሻገር ለውሃ ቱሪዝም መስፋፋት እና የውሃ ላይ ስፖርቶችን ለማልማት ትልቅ ትኩረት መስጠቱን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

ይህም የውሃ ቱሪዝም በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ያስችላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያ የሆኑት አቶ ኤንዲ አሰፋ በበኩላቸው፤ የሞተር ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲገቡ መፈቀዱ ለሀገሪቱ የውሃ ቱሪዝም ዕድገት ጠቃሚ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

ይህ ውሳኔ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ በማሻሻል ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም