ቀጥታ፡

በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የታየው ሀገራዊ አንድነት በሌሎች ልማቶችም ሊደገም ይገባል

ደሴ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፡- በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የታየው ሀገራዊ አንድነት በሌሎች  ልማቶችም ሊደገም እንደሚገባ የሐይማኖት አባቶች ተናገሩ። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቁን ተከትሎ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ዜጎች ወደ አደባባይ ጭምር በመውጣት ደስታቸውን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።

ላለፉት 14 ዓመታት የተለፋበት የህዳሴ ግድብ በብዙ ውጣ ውረድና ልፋት፤ በመንግስት ብርቱ ጥረትና በህዝቡ ያላሰለሰ ድጋፍ ለስኬት መብቃቱ ይታወቃል።

በመሆኑም አጠቃላይ የተገኘውን ሀገራዊ ስኬት በማስመልከት የኢዜአ ሪፖርተር በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ የኃይማኖት አባቶችን አነጋግሯል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት አባቶች መካከል የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ መላከ ሰላም ፈንታ አበራ፤ ኢትዮጵያዊያን የሚያምርብንና ለስኬትም የሚያበቃን ከጥንት ጀምሮ የመጣው አብሮነትና ትብብራችን ነው ብለዋል።


 

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬትም ማሳያው ይሄው መሆኑን አንስተው በግድቡ ግንባታ ሂደት የታየው ሀገራዊ አንድነት በሌሎች  ልማቶችም ሊደገም ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የህዳሴ ግድብ ለኢትየጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለጎረቤቶችና ወዳጆች ሁሉ የሚጠቅም ከሀገር የሚሻገር ፋይዳ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ዑለማ ምክር ቤት የፈትዋ ዘርፍ ኃላፊ ሸሕ ኡመር አሊ፤ የሕዳሴ ግድብ ለዘመናት የፈሰሰው ታላቁን አባይ በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት የተረጋገጠበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በኢትየጵያዊያን አንድነትና ትብብር እውን የሆነ ብሄራዊ ፕሮጀክት በመሆኑ ሁሉም ደስታውን በጋራ እየገለጸ ስለመሆኑም አንስተው ሕብረትና አብሮነትን በማስቀጠል ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችንም ማሳካት አለብን ብለዋል።

በትብብር አንድነትን አጠናክረን ከቀጠልን የማናልፈው ፈተና፣ የማንሻገረው ችግር የለም ያሉት የኃይማኖት አባቶቹ የሕዳሴ ግድብ የእድገት፣ የብርሃን፣ የለውጥና የአንድነት ተስፋ በመሆኑ ተደስተናል ሲሉ ተናግረዋል።

ከተባበርንና አንድ ከሆንን የማናልፈው ፈተና፣ የማንሻገረው ችግር አለመኖሩን ከሕዳሴ ግድቡ ተምረናል ያሉት ደግሞ የደሴ መካነየሱስ ቤተክርስቲያን መሪ ቄስ መስፍን ጌታሁን ናቸው።


 

የሕዳሴ ግድባችን የእድገት፣ የብርሃን፣ የለውጥና የአንድነት ተስፋችን በመሆኑ ደስታችን የላቀ ነው ብለዋል።

በቀጣይ የባሕር በር ጥያቄያችን መልስ እንዲያገኝ ሕብረተሰቡን በማስተባበር የድርሻችንን እንወጣለን፤  እንደ ሕዳሴ ግድባችን ተባብረን ማሳካት ከሁላችንም ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል።

በደሴ ከተማ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ   መካሄዱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም