ቀጥታ፡

 ጠንክሬ በመስራቴ ባገኘሁት ውጤት ተደስቻለሁ  

ድሬደዋ፤ መስከረም 8/2018 (ኢዜአ)፦ለዓላማዋ ስኬታማነት  ጠንክራ በመስራቷ ባገኘችው ውጤት መደሰቷን በድሬዳዋ የእመቤታችን ትምህርት ቤት ተማሪ አፎሚያ ጋሹ ገለጸች።

በ2017ዓ.ም የተሰጠውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡት መካከል በድሬዳዋ የእመቤታችን ትምህርት ቤት ተማሪ  የሆነችው   አፎሚያ ጋሹ  አንዷ ናት።

ተማሪዋ  ጎበዝ፣ በስነምግባር የታነፀችና  ለሌሎች ተማሪዎች አርአያ  በመሆኗ ያመጣችው ውጤት የሚጠበቅ መሆኑን የገለጹት ደግሞ መምህራኖቿ ናቸው።

የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ተማሪዎች ውጤታቸውን በይፋ አውቀው ቀጣይ መዳረሻቸውን እያማተሩ ናቸው።

ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ድሬዳዋ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡት መካከል የእመቤታችን ትምህርት ቤት ተማሪዋ አፎሚያ ጋሹ ተጠቃሽ ናት።

ተማሪዋ ከ600 ጥቅል የምዘና ጣራ 574 በማምጣት  ከድሬዳዋ ግንባር ቀደም  መሆን  ችላለች።

ተማሪ አፎሚያ ጋሹ ያስመዘገበችው ውጤት ጠንክራ በመስራቷ ያገኘችው የልፏቷ ውጤት መሆኑን  ለኢዜአ ገልፃለች።

የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለትምህርት ዕውቀቷ መጎልበት እንደምትጠቀም ጠቅሳ፤  ትምህርቷን በጥብቅ ስነምግባር መከታተሏ ለውጤቷ ማማር እንዳገዟት አንስታለች።

የወላጆቿና የመምህራን ክትትልና ድጋፍ ለውጤቷ ማማር ወሳኝ መሆኑን የገለፀችው ተማሪ አፎሚያ፤ በተለይም ሴቶች ለነገ ዓላማቸው መሳካት እና ውጤት ጊዜና ጉልበታቸውን ለትምህርት መስጠት እንዳለባቸው ተሞክሮዋን አካፍላለች።

ለቴክኖሎጂ እና ለሳይንስ ዘርፎች ከፍተኛ ፍላጎት ያላት መሆኑን የጠቀሰችው ተማሪዋ፤ በቀጣይም በእነዚህ መስኮች ላይ የተሻለ ዕውቀትና ክህሎት በመጨበጥ ከራሷና ቤተሰቦቿ አልፎ ለሀገር የሚጠቅም ስራ እንደምታሳካ ተናግራለች።

ለዓላማዬ ስኬታማነት  ጠንክሬ በመስራቴ ባገኘሁት ውጤት ተደስቻለሁ ብላለች ተማሪ አፎሚያ። 

ተማሪዎች ውጤታማ እና  ሀገር ገንቢ ትውልድ እንዲሆኑ የወላጆች ጥብቅ ድጋፍና ክትትል መሠረታዊ ሚና እንዳለው የገለፁት ደግሞ የተማሪ አፎሚያ አባት አቶ ጋሹ ሙሉ ናቸው።

ከልጅነቷ ጀምሮ ለትምህርት ልዩ ስፍራ እንድትሰጥ እና ውጤታማ እንድትሆን እንደ ወላጅ የድርሻችንን ተወጥተናል ፤ ከመምህራኖቿ ጋር የዘራነውን በጋራ በደስታ አጭደናል፤ እናም ተደስተናል  ብለዋል።

ተማሪ አፎሚያ ጋሹ በትምህርቷ ላይ ሰለቸኝ  ደከመኝን የማታውቅ ዓላማ ያላት ተማሪ መሆኗን የገለፁት ደግሞ የፊዚክስ መምህሯ እና የክፍል ተቆጣጣሪዋ መምህር ኃይለማርያም ረታ ናቸው።


 

ተማሪዋ ጥሩ ስነምግባርን ከብቃትና ታታሪነት ጋር በመያዝ  በአርአያነት የሚጠቀስ የደረጃ ተማሪ መሆኗን ገልጸዋል።

የእመቤታችን ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ-መምህር አቶ በየነ ደገፋ፤  ተማሪ አፎሚያ የላቀ ውጤት እንደምታመጣ ሁሉም የሚጠብቀው እንደነበር ተናግረዋል ።

ይህች ተማሪ  ወደፊት በቴክኖሎጂው ዘርፍ ሀገርን የሚያስጠራ የተለየ ስራ እንደምታከናውን በእርግጠኝነት መናገር እፈልጋለሁ ብለዋል።

በዘንድሮው ዓመት ተማሪዎች በስነምግባር ታንፀው ልክ እንደ ተማሪ አፎሚያ ውጤታማ እንዲሆኑ ወላጆች ከመምህራን ጋር በመቀናጀት ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም