የትጋት ተምሳሌቶች - ኢዜአ አማርኛ
የትጋት ተምሳሌቶች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018 (ኢዜአ)፦የትጋት ተምሳሌቶቹ በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ተማሪ ኃይማኖት እና ቅዱስ
የትምህርት ሚኒስቴር መስከረም 4 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በተፈጥሮ ሳይንስ ከፍተኛው ውጤት በወንዶች ከዶዶላ ኢፋ ቦሩ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት 591 በሴቶች ደግሞ ከብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት 579 ማስመዝገባቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
ከብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት 579 ውጤት ያስመዘገበችው ተማሪ ኃይማኖት ዮናስ እና ከወይዘሮ ቀለመወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከፍተኛውን 504 ነጥብ ያስመዘገበው ተማሪ ቅዱስ ተስፋዬ ልምዳቸውን አካፍለውናል፡፡
ተማሪዎቹ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ለትምህርታቸው ቅድሚያ በመስጠት ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀማቸው የተሻለ ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
በ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁለተኛውን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው የብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት ተማሪ ኃይማኖት ዮናስ ትኩረትና ጊዜን በአግባቡ መጠቀም መቻሏ ለስኬት እንዳበቃት ገልጻለች፡፡
ለትምህርቷ ቅድሚያ በመስጠት ጊዜዋን በማንበብ እንደምታሳለፍ በመግለጽ፤ የትኛውን የትምህርት ዓይነት መቼ ማጥናት እንዳለባት ቀድማ ፕሮግራም ማውጣቷንም አውስታለች፡፡
የወይዘሮ ቀለመወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ቅዱስ ተስፋዬ ለማንበብ የሚመቸኝን ጊዜ በአግባቡ እጠቀማለሁ ነው ያለው፡፡
ለትምህርት ቅድሚያ በመስጠት ትኩረትን ሰብስቦ ማንበብ ከተቻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ገልጿል፡፡
ትኩረት፣ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም፣ ፍርሃትን ማስወገድና የራስን የአጠናን ስልት መቀየስ የውጤታማነት ቁልፍ መንገዶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
መምህራን፣ የትምህርት ቤቶቹ ማህበረሰቦችና ወላጆቻቸው ድጋፍና ክትትል ላስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት የጎላ አበርክቶ እንዳለውም ገልጸዋል የትጋት ተምሳሌቶቹ ኃይማኖት እና ቅዱስ፡፡
በቀጣይ ህልማቸውን በማሳካት ሀገራቸውን ለማገልገል በትጋት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡
በወይዘሮ ቀለመወርቅ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የሂሳብ መምህር ደመቀ ወርቄ፤ ተማሪ ቅዱስ ተስፋዬ ታታሪ፣ ምስጉንና ለሌሎች ተማሪዎች አርዓያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በብስራተ ገብርኤል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል የፊዚክስ መምህር አንዷለም አየለ በበኩላቸው፤ ተማሪ ኃይማኖት ዮናስ መምህራን ለሙያው የበለጠ ፍቅር እንዲኖራቸው የምታደርግ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀችና ጎበዝ ተማሪ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
የቀለመወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ወይዘሮ ጋዲሴ ደረሰ እንዳሉት፤ ትምህርት ቤቱ ከተማሪ ቅዱስ ተስፋዬ በተጨማሪ ብዙ ተማሪዎችን እያፈራ ነው፡፡
በዚህም በቀለመ ወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው የሚያልፉ ተማሪዎች ምጣኔ በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡