በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሕዳሴ ግድብ መመረቅን በማስመልከት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሕዳሴ ግድብ መመረቅን በማስመልከት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው

አርባምንጭ/ ዲላ/ወላይታ ሶዶ ፤ መስከረም 8/2018 (ኢዜአ) :- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅን በማስመልከት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 4/ 2017 ዓ.ም መመረቁ ይታወሳል።
ይሕን በማስመልከት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡ ደስታውንና ድጋፉን ሲገልጽ ቆይቷል።
በዛሬው ዕለትም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን በጋራ እየገለጹ ይገኛሉ።
ሰልፈኞቹ የኢትዮጵያን አንድነት፣ ጥንካሬ፣ አይበገሬነትና ጀግንነት እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያወሱ የተለያዩ መልዕክቶችን እያስተላለፉ ነው።
ግድባችን የሕብረ ብሔራዊነታችንና የአንድነታችን መሠረት ነው፣ ግድባችን የኢትዮጵያ ትንሳኤ ማሳያ ነው፣ በሕብረት ችለናል ጨርሰን አሳይተናል የሚሉ መልዕክቶቹም እየተስተጋቡ ይገኛሉ።
እንዲሁም ግድቡ የመንግስት ጠንካራ አመራር ሰጪነት እና የሕብር ውጤት ነው፣ በግድቡ ላይ ያሳየነውን አንድነት በሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ላይ እንደግመዋለን በማለት ነዋሪዎቹ ደጋፋቸውን እየገለጹ ነው።