ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ስትራቴጂዎችን ወደ ተግባር በመቀየር እያከናወነች ያለው ስራ የሚደነቅ ነው -የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከፍተኛ የአየር ነብረት አስተዳደር ባለሙያ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018(ኢዜአ)፦  ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ስትራቴጂዎችን ወደ ተግባራዊ እውነታ በመቀየር እያከናወነች ያለው ስራ የሚደነቅ ነው ሲሉ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከፍተኛ የአየር ነብረት አስተዳደር ባለሙያ ጀምስ ሙሮምቤድዚ ገለጹ።

የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሴኤ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነች ላለው ስራ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። 

የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ዩኤንኢሴኤ) ከፍተኛ የአየር ነብረት አስተዳደር ባለሙያ ጀምስ ሙሮምቤድዚ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽእኖዎችን ለመከላከል አፍሪካ በቀል መፍትሄዎችን የመጠቀም ባህል ሊያድግ እንደሚገባ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም አረንጓዴ አሻራ በመላው አፍሪካ በስፋት ሊተገበር የሚገባ ኢኒሼቲቭ ነው ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለንጹህ ኢነርጂ ምንጭነት እና ለዘላቂ የኢንዱስትሪ እድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚወጣ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የካርቦን ልህቀትን  በመቀነስ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ መስክረዋል። 

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ እድገት ስትራቴጂ  ከስነ ምህዳር ማገገም፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ የካርቦት ልህቀት ቅነሳ እና የኤሌክትሪክ መኪኖች አገልግሎት እርምጃዎች ጋር ተዳምሮ ለአረንጓዴ እና ታዳሽ ኃይል ልማት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ስትራቴጂዎችን ወደ ተግባራዊ እውነታ በመቀየር እያከናወነች ያለው ስራ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ መዲና የሆነችው ኢትዮጵያ በአህጉሪቷ ውስጥ ያላት ስትራቴጂካዊ ስፍራ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በመተባበር የአየር ንብርተ መፍትሄዎችን ለመተግበር ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላትም ነው የገለጹት ከፍተኛ ባለሙያው። 

የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗም የአህጉሪቷ የአየር ንብረት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ማዕከል እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።

ባለሙያው ኢትዮጵያ እና ኢሴኤ ለረጅም ጊዜ የቆየ አጋርነት እንዳላቸው ገልጸው በአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ እና አቅም ግንባታ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ኢሲኤ ከኢትዮጵያ ተቋማት ጋር በመሆን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ግንባታን እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል። 
የአየር ሁኔታ ትንበያ እና ቅኝት ስርዓትን ማጠናከር እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ በፖሊሲ እና በትግበራ ደረጃ የመደገፍ ስራ መኖሩንም ጠቅሰዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም