ቀጥታ፡

በመደመር እሳቤ የህዳሴን ግድብ የመሰሉ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ትብብራችንን ልናጠናክር ይገባል

ሚዛን አማን፤ መስከረም 7/2018 (ኢዜአ)፡- በመደመር እሳቤ የህዳሴን ግድብ የመሰሉ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለማሳካት በትብብር መንቀሳቀሱ ሊጠናከር እንደሚገባ ተመላከተ። 

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ መመረቅ ተከትሎ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄዷል።

በሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ መሠረተ ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጅዮ ሳፒ እንዳሉት፤ በመደመር እሳቤ የህዳሴን ግድብ የመሰሉ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ትብብራችንን ልናጠናክር ይገባል። 


 

ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፈጠረውን መነቃቃት በሁሉም አካባቢ ሊጎለብትና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ሊውል ይገባል ብለዋል።

''የደምና የላብ ዋጋ የተከፈለበት የጋራ አሻራችን የሆነው ሕዳሴን መድገም ቀጣዩ ራእያችን ይሆናል'' ሲሉ ገልጸዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በበኩላቸው ወደ ሥልጣኔ ማማ ለመድረስ የተፈጥሮ ሀብታችንን አልምቶ መጠቀም መጀመራችን ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።


 

የብልጽግና ጉዞ አመላካች የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከልማት ባሻገር የአገራዊ መግባባት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

አንድነታችን ፈተናን መሻገርያ ምርኩዛችን በመሆኑ የማይቻሉ የሚመስሉ ጉዳዮችን ችለን ለዓለም ማሳየታችንን መቀጠል አለብን ነው ያሉት።

በይቻላል መንፈስ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት የተቀየረው ዓባይ ታሪክ ከመናገር ታሪክ ወደ መሥራት እንድንሸጋገር አድርጎናል ያሉት ደግሞ የሚዛን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሰሎሞን ሌዊ ናቸው።


 

በሰልፉ ላይ ከተገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ተስፋዬ ማሞ የግድቡ መመረቅ  የመቻል ምልክት መሆኑን ተናግረዋል።


 

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ላለፉት 14 ዓመታት ካላቸው ቀንሰው እያዋጡ አንድነታቸውን ያጸኑበት መሆኑን ገልጸው በቀጣይ መንግሥት የሚያስጀምራቸውን ፕሮጀክቶች በተሻለ መልኩ ለመደገፍ አነሳስቶናል ብለዋል።


 

ወይዘሮ ብርሃኔ ወርቁ በበኩላቸው በመተባበር የጀመርነው የሕዳሴ ግድብ መመረቁ፤ ጀምሮ ለመጨረስ አንድነት ትልቅ አቅም መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም