ብርሃኔ አደሬ - ኢትዮጵያን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለበርካታ ጊዜ የወከለች አትሌት - ኢዜአ አማርኛ
ብርሃኔ አደሬ - ኢትዮጵያን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለበርካታ ጊዜ የወከለች አትሌት

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1983 በፊንላንድ ሄልሲኒኪ ከተካሄደው የመጀመሪያው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አንስቶ በተካሄዱት ውድድሮች ላይ በሙሉ ተሳትፋለች።
በነዚህ ሻምፒዮናዎች ላይ በርካታ አትሌቶች የኢትዮጵያ ስም እና ባንዲራ ከፍ ያደረጉ ገድሎችን ሰርተዋል።
አትሌት ብርሃኔ አደሬ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲነሳ ሁሌም አብራ እንድትነሳ የሚያደርግ ታሪክ አላት።
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን በመወከልና ብዙ ጊዜ በመሳተፍ የአጠቃላይ ቀዳሚነቱን ደረጃ የያዘችው ብርሃኔ አደሬ ናት።
ብርሃኔ ከእ.አ.አ 1993 እስከ 2005 በተካሄዱ ሰባት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ ተሳትፋለች።
አትሌቷ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ያደረገችው እ.አ.አ በ1993 በጀርመን ስቱትጋርት በተካሄደው አራተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ነበር።
በ10000 ሜትር ሴቶች ውድድር ማጣሪያ ተሳትፋ ለፍጻሜው ማለፍ አልቻለችም።
በስዊድን ጉተንበርግ እ.አ.አ በ1995 በተካሄደው አምስተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10000 ሜትር ሴቶች ብትወዳደርም ማጣሪያውን አላለፈችም።
ብርሃኔ እ.አ.አ በ1997 በግሪክ አቴንስ በተካሄደው ስድስተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10000 ሜትር ፍጻሜ ተወዳድራ አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
31 ደቂቃ ከ49 ሴኮንድ ከ17 ማይክሮ ሴኮንድ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ ነበር።
በስፔን ሲቪያ እ.አ.አ በ1999 በተካሄደው ሰባተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በድጋሚ በ10000 ሜትር ፍጻሜ ተወዳድራ 31 ደቂቃ ከ29 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ ሰባተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
አትሌት ብርሃኔ የመጀመሪያ ሜዳሊያዋን ያገኘችው እ.አ.አ በ2001 በካናዳ ኤድመንተን በተደረገው ስምንተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነው።
አትሌቷ በ10000 ሜትር ፍጻሜ 31 ደቂቃ ከ48 ሴኮንድ ከ85 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።
በውድድሩ የወርቅ ሜዳሊያውን ያገኘችው አትሌት ደራርቱ ቱሉ ነበረች።
እ.አ.አ በ2003 በፈረንሳይ ፓሪስ የተካሄደው ዘጠነኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለብርሃኔ ትልቁን ስኬት ያገኝችበት ሆኖ አልፏል።
አትሌት ብርሃኔ በ10000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ 30 ደቂቃ ከ04 ሴኮንድ ከ18 ማይክሮ ሴኮንድ የወርቅ ሜዳሊያ አገኝታለች። በርቀቱ የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን አሻሽላለች።
በወቅቱ በ5000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ተሳትፋ 10ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ብርሃኔ የመጨረሻ የሻምፒዮና ተሳትፏዋን ያደረገችው እ.አ.አ በ2005 በፊንላንድ ሄልሲንኪ በተካሄደው 10ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ነበር።
በ10000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን ተከትላ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አገኝታለች።
30 ደቂቃ ከ25 ሴኮንድ ከ41 ማይክሮ ሴኮንድ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ ነበር።
አትሌት ብርሃኔ አደሬ በሻምፒዮናው ተሳትፎ አንድ የወርቅ እና ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
አትሌቷ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይም ኢትዮጵያን ወክላ ተወዳድራለች።
ብርሃኔ ራሷን ከውድድር ከማግለሏ በፊት በግማሽ ማራቶን እና ማራቶን ውድድሮች ላይ ተሳትፎ አድርጋለች።
አትሌት ብርሃኔ አደሬ እና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁሌም ሲወሳ የሚኖሩ የታሪክ ትስስሮሽ አላቸው።