የመደመር መንግሥት ማደግ ለሚፈልጉ ሀገራት እጅግ አስፈላጊ ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት ማደግ ለሚፈልጉ ሀገራት እጅግ አስፈላጊ ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2018 (ኢዜአ)፡- የመደመር መንግሥት መጽሐፍ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ማደግና መለወጥ ለሚፈልጉ ሀገራት በሙሉ እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈው “የመደመር መንግሥት” መጽሐፍ ተመርቋል።
በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር የመደመር መንግሥት መጽሐፍ፤ ጊዜ ተሰጥቶናል በግልጽ ምልከታና እሳቤ ሀገራችንን ብንሠራ ታሪክ ሠሪዎች እንጂ ዘካሪዎች አንሆንም በሚል የተዘጋጀ ሠነድ ነው ብለዋል።
ይህም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ማደግና መለወጥ ለሚፈልጉ ሀገራት በሙሉ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት ማጠንጠኛው “አራት መ” መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ የመጀመሪያው “መ” መነሻ ነው ብለዋል። መነሻውም ቁጭት መሆኑን ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያ ለምን ድሃ ሆነች? ኢትዮጵያ ለምን ተረጂ ሆነች? ኢትዮጵያ ከማን ስለምታንስ ነው ከማን የምትረዳው? የሚሉ የቁጭት ጥያቄዎች እና ምክንያት ፍለጋ ነው መነሻው ብለዋል።
አሳማኝ ምክንያት ካልተገኘለት ቁጭት ያንገበግባል፤ እንቅልፍ ይነሳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ለመደመር መንግሥት መነሻ ሆኗል ሲሉም ገልጸዋል።
ምንም እንኳን በርካታ ድሃ ሀገራት ቢኖሩም የኢትዮጵያ ድሃ መሆን የሚያንገበግበው ግን፤ ምድረ ቀደምት መሆኗ፣ የነጻነት ገድል ያላት፣ በባህልና በታሪክ የሚያኮራ ሥራ ያላት በመሆኗ ነው ብለዋል።
እንደ ምድረ ቀደምትነት የግብርና ሥራን ቀድመን ብንጀምርም፤ እስካሁን አሠራራችን በሚፈለገው ልክ በቴክኖሎጂ አለማደጉ ይቆጫል።
በሽመና እንዲሁም በባህል መድኃኒት ነባር ልምድ ያለን ሀገር እንዴት በስፋት ማምረት እና ራሳችንን መቻል ተሳነን? የሚል ቁጭት መነሻ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከቁጭት በተጨማሪ መንፈሳዊ ቅናት ለመደመር መንግሥት መነሻ እንደሆነም አብራርተዋል።
የመደመር መንግሥት ከተገነዘባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል፤ የተዛቡ ጥያቄዎች መኖር እና ለዚህም ደግሞ አፍራሽ የለውጥ ሂደት መከተል የሚሉት ይገኙበታል ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ አንድ መንግሥትና ግለሰብ ስኬት ሳይሆን፤ የመላ ኢትዮጵያውን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ገድል መሆኑንም አስረድተዋል።