የእኛ መሻት የምትመሰል ሀገር መፍጠር ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የእኛ መሻት የምትመሰል ሀገር መፍጠር ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2018 (ኢዜአ)፡- የእኛ መሻት የምትመስል ሳይሆን የምትመሰል ሀገር መፍጠር ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈው “የመደመር መንግሥት” መጽሐፍ ተመርቋል።
በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ የመደመር መንግሥት ውጤት ከሰማነው፣ ካነበብነው ብቻ ሳይሆን በተግባር ስንሞክር ካየነው ውጣ ውረድ ጭምር የተቀዳ ነው ብለዋል።
በዚህም ብዙዎች የሚማሩበት፣ የሚያሳድጉት፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማየት የሚተጉበት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም ነው ያሉት።
የመፈጸም ብቃታችንን በብዙ መንገድ ዐይተናል፤ የእኛ መሻት የምትመስል ሀገር ሳይሆን የምትመሰል ሀገር መፍጠር ነው ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል።
ብዙ ጊዜ ለመምሰል ሞክረን አልተሳካም፤ አሁን በእኛ መልክ፣ በእኛ እሳቤ፣ በእኛ ባህል ልክ ተቀርጾ በምሳሌነት የሚወሰድ ሀገር መገንባት እንፈልጋለን ሲሉም ተናግረዋል።
ይህ እንደሚቻልም የመደመር መንግሥት በጽኑ ያምናል ሲሉ አስረድተዋል።
ለአብነትም የአረንጓዴ ዐሻራን ሥራ ጠቅሰው፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ 48 ቢሊየን ችግኝ መትከል በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ማንም ያልሞከረው መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የምንመሰልበት ሆኖ በታሪክ ማኅደር ይቀመጣል ነው ያሉት በንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
እንዲሁም በትጋትና በቅንጅት ያሰብነውን ማሳካት እንደምንችል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።