ማህበረሰቡ ስለ ታክስና ጉምሩክ ስርዓት ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የቅንጅት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበረሰቡ ስለ ታክስና ጉምሩክ ስርዓት ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የቅንጅት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፡-ማህበረሰቡ ስለ ታክስና ጉምሩክ ስርዓት ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የቅንጅት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ገለፁ።
"የታክስና ጉምሩክ እውቀት ለህግ ተገዢነት መሰረት ነው" በሚል መሪ ሀሳብ በታክስና ጉምሩክ ዙሪያ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የተማሪዎች የአሸናፊዎች አሸናፊ የጥያቄና መልስ ውድድር ተካሂዷል።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በዚሁ ወቅት የማህበረሰቡን የታክስ ግንዛቤ ለማሳደግ ስትራቴጂክ እቅድ ተነድፎ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የታክስ እና ቀረጥ አከፋፈል ላይ የህግና አሰራር ስርዓት ማሻሻያ በማድረግ በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን አንስተው፥ ይህንን አስፍቶ ለማስቀጠል የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልዶች ላይ ስለ ታክስ ሀገራዊ ፋይዳ በቂ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የውድድሩ ተሳታፊና አሸናፊ ተማሪዎች ያገኙትን የታክስ እውቀት ለትምህርት ቤት ጓደኞቻቸውና ለአካባቢያቸው ማህበረሰብ ተደራሽ እንዲያደርጉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህ አኳያ ከትምህርት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተተኪው ትውልድና ማህበረሰቡ የታክስና ጉምሩክ ስርዓትን በተመለከተ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ የቅንጅት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ማህበረሰቡ ስለታክስና ጉምሩክ በቂ ግንዛቤ ኖሮት ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
በታክስና ጉምሩክ ስርዓት ዙሪያ በተዘጋጀው ሀገራዊ ውድድር ከ320 በላይ ትምህርት ቤቶች ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደተሳተፉበት ገልጸዋል።
በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካል ግንዛቤ የማስፋትና ህገወጥነትን የመከላከል ሃላፊነትን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በውድድሩ ከ1ኛ እስክ ሦስተኛ የወጡት ተማሪዎች በበኩላቸው፥ ስለታክስና ጉምሩክ በተሰጣቸው ስልጠና በቂ ግንዛቤ መቅሰማቸውን ተናግረዋል።
የግንዛቤ መፍጠሪያና የውድድር መርሃ ግብሮች ተጠናክረው መቀጠላቸው ትውልዱ ስለ ታክስ ሀገራዊ ፋይዳ በቂ እውቀት እንዲኖረውና ሀገሩን በታማኝነት እንዲያገለግል ያስችላሉ ብለዋል።
የታክስና ቀረጥ ህግን ለማስከበር፣ ህገወጥነትን ለመከላከልና ግንዛቤን ለማስፋት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ጠቁመዋል።
በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ለወጡ ተማሪዎች፣ ለአሰልጣኝ መምህራን እና ለትምህርት ቤቶች የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።