ቀጥታ፡

ለህፃናትና ጨቅላ ህፃናት የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አምጥተዋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፡-ለህፃናትና ጨቅላ ህፃናት ከውልደት ጀምሮ  የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ማስገኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የዓለም የህሙማን ደህንነት ቀን "ደህንነቱን የጠበቀ የጤና ክብካቤ ለሁሉም ጨቅላ ህፃናት እና ህፃናት "በሚል መሪ  ሃሳብ  በአለርት ሆስፒታል ተከብሯል።


 

በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ የህፃናትና ጨቅላ ህፃናትን ደህንነት ለመጠበቅ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

ለአብነትም የጨቅላ ህፃናትና ህፃናት የጽኑ ህሙማን ክፍል፣ ማሞቂያ ስፍራ እና የህክምና ግብአትን ከማሟላት አንፃር በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ነው ያነሱት።

ከውልደት ጀምሮ የሚሰጡ የህክምና፣ የክትባትና ሌሎች የጤና አገልግሎቶች ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ መደረጋቸው ለተገኘው ውጤት መሰረት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የህፃናትና ጨቅላ ህፃናት አገልግሎት በሁሉም ጤና ተቋማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጤና ሚኒስቴር በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ናምቢያር ቤጆይ በበኩላቸው፤ የታካሚዎችን ደህንነት መጠበቅና ለህፃናት ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ እንክብካቤ በማድረግ ደህንነታቸውን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሽመልስ ገዛኸኝ በበኩላቸው ሆስፒታሉ የህሙማንን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።


 

በዚህም ታካሚዎች ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ ደህንነታቸው ተጠብቆ የሚፈልጉትን አገልግሎት በፍጥነት እንዲያገኙ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም