የታላቁ የህዳሴ ግድብ ስኬት በቀጣይ ለሚከናወኑ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መሠረት የጣለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ስኬት በቀጣይ ለሚከናወኑ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መሠረት የጣለ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ስኬት በቀጣይ ለሚከናወኑ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መሠረት የጣለና ኢትዮጵያ በሀብቷ የመጠቀም መብቷን በተግባር ያረጋገጠችበት መሆኑን የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን በማስመልከት የድጋፍ እና የደስታ መግለጫ ሰልፍ "በአንድነት አሳክተናል" በሚል መሪ ሃሳብ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።
የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያሳኩት እና የኢትዮጵያን ማንሰራራት ያሳየ ነው።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ በርካታ ውጣ ውረዶችን በማለፍ ለስኬት መብቃቱን ገልፀው፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የራሱን አሻራ ያሳረፈበት መሆኑን አስታውሰዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ስኬት በቀጣይ ለሚከናወኑ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መሠረት የጣለና ኢትዮጵያ በሀብቷ የመጠቀም መብቷን በተግባር ያረጋገጠችበት መሆኑን ተናግረዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ከተሳተፉት መካከል ወይዘሮ ሙሉ ሊኪሳ እንዳሉት ኢትዮጵያውያን በጋራ ከቆምን ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመስራት ከድህነት መውጣት እንደምንችል አሳይተናል ብለዋል።
ወጣት ቢኒያም ግርማ በበኩሉ የህዳሴ ግድብ ስኬት በሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ በመቆም የበኩላችንን እንድንወጣ የሚያነሳሳን ነው ሲል ተናግሯል።
ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ ደረጄ ቶሌራ በበኩሉ ህዳሴ ግድብን በጋራ ማሳካት እንደቻልን ሁሉ ሌሎች አገራዊ ፕሮጀክቶችን በትብብር ማስቀጠል አለብን ብሏል።
የግድቡ ስኬት እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ለልማት እንድናውል ትልቅ መነሳሳት ፈጥሮብናል ሲል ነው ሃሳቡን የገለጸው።
የህዳሴ ግድብን በራሳችን አቅም መገንባት መቻላችን ለዘመናት ቁጭታችን ፍጻሜ የሰጠ ነው ሲሉ የገለጹት ደግሞ በሰልፉ የተሳተፉት አባገዳ አዲሱ በልዳ ናቸው።
አቶ ደጀኔ አስፋው በበኩላቸው፤ጫናዎችን በመቋቋም ህዳሴ ግድብን በራስ አቅም ማጠናቀቃችን ለሌሎች የልማት ስራዎች ትምህርት ይሆነናል ብለዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ በህዳሴ ግድብ ግንባታ የነበራቸውን ተሳትፎ በሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በመድገም ለሀገር ዕድገት መሰረት የሚሆን ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።