የደብረ ብርሃን ከተማ ልማትን ለማስቀጠል ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የደብረ ብርሃን ከተማ ልማትን ለማስቀጠል ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ ትኩረት ተደርጓል

ደብረብርሃን ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፡- የደብረ ብርሃን ከተማን የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ ትኩረት መደረጉን የከተማው አስተዳደር ገለጸ።
የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ በ2017 ዓ.ም እቅድ አፈፃፀምና የ2018 ዓ.ም የገቢ እቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ዛሬ አካሂዷል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በመድረኩ ላይ እንደገለጹት የደብረ ብርሃን ከተማ በኢንዱስትሪ፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎች ልማቶች ተመራጭ እየሆነች መጥታለች።
''በቀጣይም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን አቅደን ለመፈጸም ገቢን አሟጠን መሰብሰብ ላይ አተኩረን መስራት አለብን'' ያሉት ከንቲባው ''በራስ አቅም የከተማችንን እድገት ለማፋጠንና የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ ይሰራል'' ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ ሃላፊ አቶ አበባየሁ ሞገስ በበኩላቸው የከተማዋን ልማት ለማፋጠን በ2018 በጀት ዓመት 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።
ከሀምሌ ወር ጀምሮ በተካሄደው የደረጃ “ሐ” ግብር ስርአት 64 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን ጠቁመው የተጠናከረ የገቢ የማሰባሰብ ስራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡም የቫት ደረሰኝ በመቀበልና ነጋዴዎችም ደረሰኝ በአግባቡ በመቁረጥና ሌሎች ህጋዊ አሰራሮችን በመከተል ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የጠባሴ ክፍለ ከተማ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሲራክ ጌታነህ፣ ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአፄ ዘራያቆብ ክፍለ ከተማ ስራ አስፈፃሚ አቶ ወንድወሰን እሸቴ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ ከህብረተሰቡ የሚነሱ የልማት ስራዎችን መመለስ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመትም የተጣለውን እቅድ ለማሳካት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር 12 ሺህ የሚጠጉ ግብር ከፋዮች መኖራቸውን የከተማው ገቢዎች መምሪያ አስታውቋል።