ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአትሌት ሲምቦ አለማየሁ  የነሐስ ሜዳሊያ አገኘች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2018 (ኢዜአ)፦ በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በሴቶች በ3000 ሜትር መሰናክል ፍጻሜ በአትሌት ሲምቦ አለማየሁ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።

አትሌት ሲምቦ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 8 ደቂቃ ከ58 ሴኮንድ ከ86 ማይክሮ ሴኮንድ ፈጅቶባታል።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሎሚ ሙለታ 9 ደቂቃ ከ14 ሴኮንድ ከ90 ማይክሮ ሴኮንድ ስምንተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። 

ኬንያዊቷ አትሌት ፌዝ ቺሮቲች 8 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ ከ59 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ የወጣች ሲሆን በርቀቱ የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን አሻሽላለች። 

በትውልድ ኬንያዊ በዜግነት ባህሬናዊ የሆነችው ዊንፍሬድ ያቪ 8 ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ ከ46 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ወጥታለች። 

በጃፓን ቶኪዮ እየተካሄደ ባለው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ እስከ አሁን ሁለት የብር እና ሁለት የነሐስ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት 13ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም