ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአንድነት ከቆምን ማንኛውንም ልማት ማሳካት እንደምንችል ያረጋገጥንበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአንድነት ከቆምን ማንኛውንም ልማት ማሳካት እንደምንችል ያረጋገጥንበት ነው

አዳማ ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአንድነት ከቆምን ማንኛውንም ልማት ማሳካት እንደምንችል ያረጋገጥንበት ነው ሲሉ የአዳማና ምስራቅ ሸዋ ዞን አመራሮችና ነዋሪዎች ገለጹ።
የአዳማ ከተማና የምስራቅ ሸዋ ዞን ነዋሪዎችና አመራሮች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቁን በማስመልከት በአዳማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ አድርገዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሀይሉ ጀልዴ ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት ግድቡ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ ለፍጻሜ መድረሱ ትልቅ ስኬት ነው።
የቀጣይ አጀንዳችን የባህር በር ጉዳይ ሊሆን ይገባል ያሉት ከንቲባው ለዚህም መንግስት ህዝቡን ከጎኑ በማሰለፍ አበክሮ ይሰራል ብለዋል።
የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍጻሜውን ማግኘቱ የብልጽግና መንግስት ትሩፋት መሆኑን አንስተዋል።
በአንድነቅ ከቆምን፣ መግባባትና መደማመጥ ከቻልን ህልሞቻችንና እቅዶቻችንን ማሳካት እንደምንችል ግድቡ ትልቅ ማስረጃ ነው በማለት በቀጣይ ሀገራችን የባህር በር እንድታገኝ ሁላችንም ልንተባበር ይገባል ብለዋል።
ከድጋፍ ሰልፉ ተካፋዮች መካከል ቄስ ዘነበ ደሳለኝ፤ በመንግስትና በህዝብ ጥንካሬ በተፈጥሮ የተሰጠንን ሀብት በራሳችን አቅም እና ሀብት የገነባነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሀገራችንን አንድነት የሚያጠናክርና የሚያኮራ ነው ብለዋል።
ግድቡ የድል አድራጊነት ከፍታችን በመሆኑ የሀገራችንን የወደብ ፍላጎት በማሳካት ልንደግመው ይገባልም ብለዋል።
ሌላኛዋ የሰልፉ ተሳታፊ ሄራን ፍቅረ በበኩሏ ግድቡ ለፍጻሜ እንዲደርስ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጓን ገልፃ ግድቡ በአዲሱ አመት በመመረቁ ልዩ ገፀ በረከት በመሆኑ ደስታ እንደተሰማት ተናግራለች።
አርቲስት ዝናሽ ሎሌም እንዲሁ ለግድቡ መሳካት በሙያዋ ህዝቡን በመቀስቀስ መሳተፏን ገልፃ በተለይም ግድቡ ሁሉንም ማህበረሰብ በአንድነት ያስተሳሰረ የህልውናችን መሠረት በመሆኑ ለፍጻሜ በመድረሱ ልዩ ደስታ እንደተሰማት ተናግራለች።