በክልሉ የከተሞችን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ፈጣን እድገታቸውን ለማስቀጠል እየተሰራ ነው -አቶ ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የከተሞችን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ፈጣን እድገታቸውን ለማስቀጠል እየተሰራ ነው -አቶ ጥላሁን ከበደ

ዲላ ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የከተሞችን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ፈጣን እድገታቸውን የማስቀጠል ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለፁ።
በክልሉ በተመረጡ ዘጠኝ ከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን ዲጂታላይዝ የማድረጊያ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በወቅቱ እንዳሉት በተያዘው አዲስ ዓመት በክልሉ የሚገኙ ከተሞችን ውስብስብ ችግሮች በመፍታት የነዋሪውን እርካታ ለማሳደግ ቅድሚያ ተሰጥቶ ይሠራል።
የኮሪደር ልማት የጎስቋላ ከተሞችን ገፅታ መቀየሩን እንደ አብነት ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህንኑ በአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት መድገም እንደሚገባም ተናግረዋል።
በተለይም በመሬት ልማት፣ በካዳስተር እና በማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ዘርፎች ትኩረት ተደርጎ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልል ደረጃ በወላይታ ሶዶ እንደሚጀመር አንስተው ይህንንም ወደ ሌሎች ከተሞች ከማስፋት ባለፈ ከዲጂታል ስርዓት ጋር በማቀናጀት ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎትን እውን ለማድረግ እንደሚሠራ ገልፀዋል።
በክልሉ በአዲሱ ዓመት በከተሞች ያለውን ውስብስብ አሰራር ለመቀየርና አገልግሎትን የማዘመን ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ናቸው።
የከተሞችን ፈጣን እድገት የሚመጥን አገልግሎት ለማቅረብ በዘጠኝ የክልሉ ከተሞች የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ዲጂታል የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
በዛሬው ዕለትም በዲላ ከተማ የተጀመረው ትግበራው በቀሩት ስምንት የክልሉ ከተሞች እንዲቀጥል በማድረግ የከተሞች ተወዳዳሪነት እንዲሰፋ ዕድልን ይፈጥራል ብለዋል።
የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን ደምሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው በከተማው የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን በማዘመን የነዋሪውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በተለይም የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ዲጂታላይዝ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎትን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
በኮሪደርና በመሠረተ ልማት ሥራዎች የተመዘገበው ውጤት ይህንን የሚያጠናክር መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የከተማ ከንቲባዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።