ቀጥታ፡

በባሕርዳር ከተማ  ከአንድ ሺህ  ለሚበልጡ  ተማሪዎች የትምሕርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ባሕርዳር ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ) ፡-  በባሕርዳር ከተማ  አስተዳደር   ድጋፍ ለሚሹ  ከአንድ ሺህ  ለሚበልጡ ተማሪዎች ዛሬ  የትምሕርት ቁሳቁስ ተበረከተ። 

የተበረከተውም  ለተማሪዎቹ በነፍስ ወከፍ  ለአንድ  ዓመት የሚበቃ የደብተር፣ እስክርብቶ፣ እርሳስና ማስመሪያ መሆኑን በርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገልጿል።


 

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር  ምክትል ከንቲባ  አቶ አስሜ ብርሌ በወቅቱ እንደተናገሩት፤  አስተዳደሩ የበጎ አድራጎት ማሕበራትና ተቋማትን በማስተባበር የትምሕርት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

የባሕርዳር በጎ አድራጎት ማሕበርም በ37 ትምሕርት ቤቶች ድጋፍ ለሚሹ  ከአንድ ሺሕ ለሚበልጡ  ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የሚበቃ  የተለያየ የትምሕርት ቁሳቁስ ድጋፍ  ማድረጉን አስታውቀዋል።


 

ከትምሕርት ቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ከ1 ሺሕ 500 በላይ እማወራና አባወራ ወገኖች የጤና መድሕን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያገዘ መሆኑንም አንስተዋል።ለተደረገውም ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ትምሕርት መምሪያ ኃላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤  የበጎ አድራጎት ማሕበሩ በየዓመቱ የትምሕርት ግብዓት ማሟላት ለማይችሉ ተማሪዎች  ድጋፍ ማድረጉ አበረታች መሆኑን  ገልጸዋል።


 

ይሕም ተማሪዎች ለትምሕርት ቁሳቁስ  ሳያስቡ ትምሕርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ  እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ማሕበሩ የትምሕርት ቤቶች ገፅታ እንዲሻሻል ደረጃውን የጠበቀ አምስት ክፍሎች ያሉት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤትና መፀዳጃ ቤቶችን ገንብቶ ማስረከቡንም አንስተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ 37 የመንግስት ትምሕርት ቤቶች ተማሪዎች የትምሕርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ የባሕርዳር በጎ አድራጎት ማሕበር ስራ አስኪያጅ አቶ አሕመድ ይማም ናቸው።


 

በማዕድ ማጋራት፣ በጤና መድሕን አገልግሎትና በሌሎችም የበጎ አድራጎት ተግባራት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ማሕበሩ  ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝና አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።


 

የተደረገልኝ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ትምሕርቴን በአግባቡ እንድከታተልና ውጤታማ እንድሆን ያግዘኛል ያለችው ደግሞ ተማሪ ኃይማኖት ፀጋዬ ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም