ቀጥታ፡

የምንደመረው ስለ አንድ ሀገር ለማሰብ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፡- የምንደመረው በአንድ ጭንቅላት ለማሰብ ሳይሆን ስለ አንድ ሀገር ለማሰብ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስገነዘቡ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተፃፈው "የመደመር መንግሥት" መፅሐፍ ትናንት ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ለሁላችንም ትበቃለች ብለዋል።

ለሀገራዊ ዕድገታችን ሁነኛው መንገድ መተባበር እና መደመር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የምንደመረው በአንድ ጭንቅላት ለማሰብ ሳይሆን ስለ አንድ ሀገር ለማሰብ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።


 

ኢትዮጵያ በምሳሌነት እንድትጠቀስ የሚያስችሉ በርካታ ራዕዮቻችንን ለማሳካት መነሻ ከያዝን፣ መዳረሻ ከአበጀን በኋላ እንዴት ባለ መንገድ መፈጸም አለብን የሚለው ትልቅ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።

ለዚህ ደግሞ በእንዴት ያለ መንገድ እንሂድ የሚለው በመደመር መንግሥት መመላከቱን አንስተዋል።

በዚህም መሠረት ራዕዮቻችንን ለማሳካት ከሚረዱ መንገዶች መካከል አንዱ ከውስጥ ወደ ውጭ መመልከት ነው ብለዋል።

በየዘርፉ የካበተ ዕውቀት ያላት ኢትዮጵያ ለማስተማር እንጂ ከሌሎች ለመማር የምትጓጓ መሆን እንደሌለባትም ጠቅሰዋል።

ያለፉን፣ የቀደሙን፣ የሰለጠኑ፣ የፈጠሩ ሀገራት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ የሚበጀንን መቅዳት ሳይሆን መማር ይጠቅማል ብለዋል።

ከሌሎች ሀገራት ስንማርም የእኛን መርምረንና አሰናስለን ግልጽ ሐሳብ መያዝ ስንችል፤ የአቅምና አቋም ድምር ስንፈጥር መሆን አለበት ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ውስጥ የአቅም እና አቋም ድምር ከፈጠርን ተዓምር መሥራት እንችላለን ሲሉም ገልጸዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም