ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዘመናችን ያሳካነው ትልቁ የልማት ውጤታችን ነው

ጊምቢ/ጭሮ/ነቀምቴ/ አምቦ ፤መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዘመናችን ያሳካነው ትልቁ  አኩሪ  የልማት ውጤታችን  ነው ሲሉ ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ የወጡ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን በማስመልክት የክልሉ ነዋሪዎች የደስታ መግለጫ ሰልፍ አካሄደዋል።

በሰልፉ የተሳተፉት የግምቢ፣ የጭሮ፣ የነቀምቴ እና የአምቦ ከተሞች ነዋሪዎች እና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዘመናችን ያሳካነው ትልቁ አኩሪ የልማት ውጤታችን  ነው ብለዋል።

በግምቢው ሰልፍ ከተሳተፉ  ነዋሪዎች መካከል አቶ ምትኩ ተስፋ እና ወጣት ጉቴ አበራ፤ ሕዳሴ ግድብ ለፍጻሜ በመብቃቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በሕዳሴ ግድብ ያሳየነው አንድነትና ትብብር በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ ለመድገም በጋራ መቆም ይገባናል ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ ከፍጻሜ እንዲደርስ በቦንድ በመግዛት የድርሻቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ  አቶ ተስፋዬ ኮርማ፤ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ የይቻላል መንፈስ እንዲጎለብት የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፈ፣ ግድቡ ሕዝቡ በተባበረ ክንድ አንድነቱን ጠብቆ ከግብ ያደረሰው በመሆኑ የዞኑ ሕዝብም ለሰላም በመፅናት  ልማት ላይም ድጋፉን በጋራ  አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ በተካሄደ ሰልፍ ላይ የተገኙት ነዋሪዎችም ግድቡ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃት ሌሎች የልማት ስራዎች ላይ በንቃት ለመሳተፍ  መነቃቃት ፈጥሮብናል ብለዋል።

ከተሳታፊዎቹ ውስጥ አቶ ከድር አሕመድ እና ወይዘሮ ፋኪያ ጀማል፤ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ  መደሰታቸውን ገልጸው፤   በሌሎች የልማት ስራዎች በንቃት ለመሳተፍ የሕዳሴ ግድብ ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገር አንድነት ከማጠናከር ባለፈ በራስ አቅም መልማት እንደሚቻል ትምሕርት የተገኘበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያሳየውን  አንድነትና ሕብረት  በሌሎች የልማት ተግባራት ላይ  ሊደግም እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢክረም ጠሀ ናቸው። 

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሕዝቦችን አንድነት ይበልጥ በማቀራረብ  ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አንሰተው፤ ሕብረተሰቡ ይሕንኑ  አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይ በነቀምቴ ከተማ በተካሄደ ሰልፍ  ከተሳተፉ  ነዋሪዎች መካከል አቶ ወዬሳ ሂረጳ፤ ግድቡ ሕብረተሰቡ ካለው በመለገስ ለነገው የሀገር  ተረካቢ ትውልድ ጠንካራ የልማት መሰረት ለማኖር ያለው ቁርጠኝነት ያሳየበት ነው ብለዋል።

ሌላኛው የነቀምቴ ነዋሪ አቶ ተመስገን ገርባ፤ የሁሉም ማሕበረሰብ ተሳትፎ ውጤት የሆነው የአባይ ግድብ ለሌሎች የልማት ስራዎችም ያነሳሳን ነው ብለዋል።

የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር አቶ ወጋሪ ነገራ በሰልፉ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልእክት፤ ለመጪው ትውልድ የተሻለ ነገ ለመፍጠር የአባይ ግድብ ግንባታ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።

የግድቡ መጠናቀቅ ሕብረተሰቡ አሁን ያገኘውን ሰላም በማፅናት የተጀመሩትን ትላልቅ ፕሮጀክቶች ለመደገፍ የተነሳሳበት ነው ያሉት ደግሞ በአምቦ ከተማ በተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙት  አቶ ኮርሳ ጫላ እና  አቶ በዳዳ ዋቅጅራ ናቸው። 

በሰልፉ ላይ የተገኙት የምዕራብ ሸዋ ዋና አስተዳደር አቶ ዲዳ ጉደታ በበኩላቸው፤  የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁ የሕዝባችንን  አንድነትና አብሮነት ያሳየ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀጫሉ ገመቹ፤ ግድባችን የሀብታችንና የክብራችን ምልክት ነው፤ በሕዝቡም ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃት የፈጠረ ነው ሲሉ   ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም