የመደመር መንግሥት በጋራ ራዕይ ላይ መሰባሰብ እንደሚያስፈልግ ያምናል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት በጋራ ራዕይ ላይ መሰባሰብ እንደሚያስፈልግ ያምናል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፡- የመደመር መንግሥት በጋራ ራዕይ ላይ መሰባሰብ እንደሚያስፈልግ ያምናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተፃፈው "የመደመር መንግሥት" መፅሐፍ ትናንት ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።
በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግርም፤ የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያውያንን በጋራ ራዕይ ላይ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ ያምናል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በጋራ ራዕይ ላይ ከተሰባሰቡ በኋላ፤ ስብራት ለይተን መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የእድገት ጉዞ እና የፖለቲካ ችግር ስብራት የጠላቶቻችን አጀንዳ የሆነው መለያየት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ መፈወሻ መድኃኒቱ ደግሞ መደመር ብቻ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በጋራ መቆም ብንችል መፍጠን እንችላለን፤ መፍጠር እንችላለን፤ በአስፈላጊው ቦታ ደግሞ መከተል ሳይሆን መዝለል እንችላለን ነው ያሉት።
አክለውም በጋራ ስንቆም ከተቀባይነትና ተከታይነት መላቀቅ እንችላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሐሳብ ተቀብለን፣ ገንዘብ ተቀብለን፣ ተልዕኮ ተቀብለን ኢትዮጵያ ላይ መለማመድ ተገቢ አይደለም በማለት በአጽንኦት ገልጸዋል።
በሥነ-ልቦና ስብራት መኖሩንና ጥሩ ነገሮች ሲታዩ የኢትዮጵያ እንደሆነ ያለመቀበል ተገቢነት የሌለው ልምምድ መኖሩንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ እንደምትችል እና በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን መቀበል እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መክረዋል።