የህዳሴ ግድብ የረጅም ዓመታት የልማት ጥረት ስኬትና የሀገር የማንሰራራት ጉዞ ጅማሬ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ የረጅም ዓመታት የልማት ጥረት ስኬትና የሀገር የማንሰራራት ጉዞ ጅማሬ ነው

ወላይታሶዶ ፤መስከረም 7/2017 (ኢዜአ):- የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የረጅም ዓመታት የልማት ጥረት ስኬትና የሀገር የማንሰራራት ጉዞ ጅማሬ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ተፈሪ አባተ ተናገሩ።
የህዳሴ ግድብ መመረቁን አስመልክቶ በወላይታ ሶዶ ከተማ የውይይት መድረክና የፎቶ አውደ ርእይ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊና የወላይታ ሶዶ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ተፈሪ አባተ፤ የህዳሴ ግድብ የረጅም ዓመታት የልማት ጥረት ስኬትና የሀገር የማንሰራራት ጉዞ ጅማሬ መሆኑን ገልጸዋል።
የዘመናት ቁጭት ያበቃበት፤ ከድህነት አዙሪት የመውጣት ጥረት እየተሳካ መሆኑ በተግባር የተገለጠበት የኢትዮጵያን ብልፅግና አይቀሬነት ማረጋገጫ መሆኑንም አንስተዋል።
በግድቡ ግንባታ ሂደት እንደ ሀገር በነበረው ርብርብ የክልሉ ህዝብ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ ብዙ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውሰው ለውጤት በመብቃቱ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ፤ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ ስኬት ትላልቅ ፕሮጀከቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን ገንብተን ማጠናቀቅ እንደምንችል በተግባር ያረጋገጥንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም አባይን በመገደብ የዘመናት የበይ ተመልካችነትና ቁጭት አብቅቶ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጊዜ እውን የሆነበት ነው ብለዋል።
በመድረኩ የክልል፣ የዞን፣ የከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎችና ምሁራን እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።