ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የሀገርን ሙሉ አቅሞች በጋራ ህልም በማስተባበር ለአንድ ዓላማ እንዲተጉ የሚያደርግ ነው - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፦ የመደመር መንግሥት የሀገርን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑ የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍና የማህበረሰቡን ሙሉ አቅሞች በጋራ ህልም በማስተባበር ለአንድ ዓላማ እንዲተጉ የሚያደርግ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተፃፈው "የመደመር መንግሥት" መፅሐፍ ትናንት ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) የመደመር መንግሥት ከፖለቲካ ኢኮኖሚ አንጻር ያለውን ዕይታ በሚመለከት ዳሰሳ አቅርበዋል።

ፀሐፊው በመደመር መንግስት መፅሐፍ እንዴት ኋላ ቀረን፣ ከዓለም ጋር የት ላይ ተላለፍን ብለው በቁጭት በመጠየቅ ችግሮችንና ስብራቶችን ለመሻገር ከውስጥ ወደ ውጭ ማየት አለብን ማለታቸውን አስቀምጠዋል።

ድክመትና ስህተታችንን ገርቶ ሀገራችንን ወደሚገባት ከፍታ እና ህዝባችንን ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማድረስ ምን ዓይነት መንግሥት ያስፈልገናል የሚለውን በግልፅ ማብራራታቸውን ነው ያነሱት።

ፀሐፊው የመደመር መንግሥትን ለመጻፍ መነሻ የሆናቸው ቁጭት ነው ያሉት ዶክተር ፍጹም፥ የዓባይን ልጅ ለምን ውሃ ጠማው በሚል ማንሳታቸውን በዋቢነት ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ለስብራቶቻችንና ኋላ ለመቅረታችን ከውጭ በቀጥታ የተቀዱ ርዕዮቶችን እንደ ቀኖና የማየት ችግርን በምክንያትነት ማንሳታቸውንም ነው የተናገሩት።


 

ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ትርምሶች ከውጪ ያገኘነውን ርዕዮተ ዓለማዊ እውቀት ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በደፈናው በማላተም የተፈጠረ ችግር ነው የሚል ዕይታ እንዳላቸውም አውስተዋል።

በመደመር መንግሥት መፅሐፍ ከምስራቁም ይሁን ከምዕራቡ የምንማራቸው ነገሮች ቢኖሩም የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ያደረገ መፍትሔ፣ መንገድና ማሳኪያ ስልት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል ነው ያሉት።

ዋናው ጥያቄ የእነዚህ ርዕዮት አቀንቃኞች እንዴት ሰለጠኑ ሳይሆን እኛ እንዴት ኋላ ቀረን መሆን አለበት ስለማለታቸውም እንዲሁ።

የመደመር መንግሥት ሦስት ጊዜ መብላት ከሚለው በእጅጉ የሚልቅ ምናባዊ ከፍታ፣ አሻጋሪ የሆኑ ህልሞችን እንደ ርዕይ መያዙን ገልጸዋል።

በኢኮኖሚው መስክም የመደመር መንግሥት የግልና የመንግሥት የኢኮኖሚ ሚናዎችን የሚገነዘብበት መንገድ የተለየ መሆኑን ዶክተር ፍጹም ተናግረዋል።

እሳቤው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ የመንግሥትና የግል ከሚለው ክፍፍል በመውጣት የሁለቱንም ዘርፎች የስራ አካሄድ እንዴት መከናወን አለበት በሚለው ላይ ያተኮራል ነው ያሉት።

የመደመር መንግሥት ሚና አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን በሚፈጥር የፈጠራ ብቃት ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል።

የመደመር መንግሥት የሀገርን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑ የሀገርን ሙሉ አቅም መንግሥትን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ የግል ዘርፉን፣ ማህበረሰቡን በጋራ ህልም በማስተባበር ለአንድ ዓላማ እንዲተጉ የሚያደርግ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ፀሐፊው ወደ ኋላ ለመቅረታችን ሥርዓታዊ ፈተና፣ የባህል ስብራትና የተቋማት ድክመትን በምክንያትነት ማንሳታቸውን ጠቅሰዋል።

የዳበረ ሥርዓት ወደ ዕድገት፣ ወደ ሙላት፣ ወደ መረጋጋትና ወደ ተገማች ውጤት ያመራል ማለታቸውንም አንስተዋል።

የመደመር መንግሥት ሥርዓታዊ ፍጥነት፣ ፈጠራና ዝላይን ሀገርን ማሻገሪያ መንገዶች ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም