በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ከደስታ የተሻገረ በመተባበር የመፈጸም አቅምን የሚያሳይ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ከደስታ የተሻገረ በመተባበር የመፈጸም አቅምን የሚያሳይ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ከደስታ የተሻገረ በመተባበር የመፈጸም አቅምን የሚያሳይ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የድጋፍ ሰልፉን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ተፈጥሮን እንደ ዐይኑ ብሌን መንከባከብ እና ማልማት ለሚያውቀው የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ሕዳሴ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል።
ውሃ ለኦሮሞ በሕይወቱ፣ በባህሉ፣ በታሪኩና በሕዝባዊ እሴቶቹ ሁሉ ትልቅ ቁርኝት ያለው የማንነት ቀለሙ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በታላቁ ወንዛችን ዓባይ ላይ ለተገነባው የህዳሴ ግድብ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ከደስታ የተሻገረ በመተባበር የመፈጸም አቅምን እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።
በድጋፍ ሰልፎቹ የተስተጋቡት ድምጾችም ልማትን የመናፈቅ ሰላምን አብዝቶ የመፈለግ፣ በመደመር የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን በብዙ ድሎች የማጽናት ብርቱ መሻቶች እንደሆኑ ለማየት ተችሏል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።