ቀጥታ፡

በትምህርት የውጤታማነት ሚስጥሩ ክፍል ውስጥ በንቃት መከታተልና ጠንክሮ ማጥናት ነው

ጅግጅጋ፤ መስከረም 7/2018 (ኢዜአ)፡- በትምህርት የውጤታማነት ሚስጥሩ ክፍል ውስጥ በንቃት መከታተልና ጠንክሮ ማጥናት መሆኑን በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከሶማሌ ክልል ከፍተኛውን ውጤት ያመጣው ተማሪ ሀምዛ ሻም መሐመድ ገለጸ።

በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች መኖራቸው ይታወቃል።

በዚህም መሰረት በዘንድሮው ፈተና 549 ነጥብ በማምጣት በሶማሌ ክልል ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው በጅግጅጋ ከተማ ዘ ስፓርክ ትምህርት ቤት የተማረው ተማሪ ሀምዛ ሻም መሐመድ ሆኗል።

ለዚህ ውጤት የበቃበትን ምክንያት የኢዜአ ሪፖርተር በጅግጅጋ በመገኘት ተማሪውን አነጋግሮታል።

በመጣው ውጤት ደስተኛ መሆኑን የተናገረው ተማሪ ሃምዛ በትምህርት የውጤታማነት ሚስጥሩ ክፍል ውስጥ በንቃት መከታተልና ጠንክሮ ማጥናት መሆኑን ገልጿል።

ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ሆኖ ጥያቄ በማዘጋጀት እንደሚሰሩና በመምህራኑ የሚሰጡትን የቤትና የክፍል ሥራዎችን በጊዜ ሰርቶ እንደሚያጠናቅቅም ገልጽዋል። 

መምህራኑ ተጨማሪ የቱቶሪያል ክፍሎች እንደሚያስተምሯቸው ገልጾ፤ ጥሩ የሥነ ልቦና ምክርም እንደሚሰጧቸው ተናግሯል።

ተማሪዎች ቤተመጻህፍት በአግባቡ ከተጠቀሙና የሚሰጡ የማጣቀሻ ምንባቦችን (ጋይድላይኖችን) በርትተው ካነበቡ ውጤታማ እንደሚሆኑም መክሯል።

በግል ጥረቴ ለስኬት ከመትጋቴም ባለፈ የመምህራኖቼ እገዛና የወላጆቼም ድጋፍ ያልተለየኝ በመሆኑ ውጤታማ ሆኟለሁ ብሏል ተማሪ ሀምዛ።

የአሁኑ ውጤት ማምጣት ብቻ በቂ ባለመሆኑና በቀጣይ ብዙ ፈተናዎች ይኖራሉ ያለው ተማሪው በአሸናፊነት በስኬት ለመዝለቅ መዘጋጀቱን አረጋግጧል።

በጅግጅጋ የዘ ስፓርክ ትምህርት ቤት ዘንድሮ ያስፈተናቸውን 25 ተማሪዎች በሙሉ ማሳለፍ የቻለ መሆኑም ታውቋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም