ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር የጎላ ሚና ይኖረዋል

አርባ ምንጭ፤ መስከረም 7/2018 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተመላከተ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ክላስተር "በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሃሳብ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ በወቅቱ እንዳሉት፤ ግድባችን የህብረ- ብሔራዊ አንድነታችን መሠረት ነው።


 

የሁሉም ኢትዮጵያውያን ገንዘብ፣ ዕውቀትና የላብ አሻራ ያረፈበት የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ከማረጋገጥ ባለፈ የቀጠናውን ሀገራት ትስስር ለማጠናከር የጎላ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

የክልሉ ህዝብ በግድቡ መጠናቀቅ የተፈጠረውን ሀገራዊ መነቃቃትና ህዝባዊ ተሳትፎ በሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መድገም እንዳለበትም አሳስበዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ  መስፍን መንዛ (ዶ/ር) በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ ዳግማዊ አድዋን መትከል ችለናል ብለዋል።


 

የወል ስኬታችንና የድል ብስራት የሆነው ግድባችን የአንድነት፣ የጽናት፣ የብርታትና የአይበገሬነት መገለጫችን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ግድቡ የኢትዮጵያ ህዝብ ብሔራዊ ጥቅሙን በልማት አርበኝነት ማረጋገጥ እንደሚችል ያሳየበት መሆኑን ጠቅሰው፤  በሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይም የህዝቡን ተሳትፎ የማጠናከር ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ከጂኦ ስትራቴጂያዊ ኩስመና ወደ ታደሰ ቁመና ያሸጋገረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በፓናል ውይይቱ ላይ የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የክልሉ ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ  ቦጋለ ቦሻ (ዶ/ር) ናቸው።

ግድቡ የዘመናት እልህና እንጉርጉሮን ወደ መልካም ፍሬ የቀየረ ከመሆኑም በላይ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ በየጊዜው የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ የቀነሰ መሆኑንም አስረድተዋል።

በውይይቱ ላይም የክልል፣ የዞንና የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች፣ የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም